ከ70 ዓመታት በላይ የሆነው የ‹‹አዊ የፈረስ ማህበር›› ባህሉን ጠብቆ በማቆየቱ በ‹‹ቅርስና ባህል ዘርፍ›› ለዘንድሮው የ‹በጎ ሰው ሽልማት› ከተመረጡ ሶስት ዕጩዎች አንዱ ሁኗል፡፡ የፈረስ ጉግስ ባህሉ ዝም ብሎ ለመዝናኛ የሚሆን ብቻ አይደለም፡፡ የማህበራዊ ስነ-ሰብ አጥኝዎች በአግባቡ ባያጠኑትም ቅሉ፣ የራሱ ታሪካዊ አመጣጥ አለው፡፡ ከታሪካዊ እውነታዎች እና አሁን የፈረስ ጉግስ ከሚዘወተርባቸው ሁነቶች ተነስቶ ሶስት መላምቶችን መገመት ይቻላል፡፡
1ኛ) አንደኛው ከመከረኛው ጦርነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡
መኪና፣ አውሮፕላን እና ዘመናዊ የጦር መሳሪያ በሌለበት ዘመን አብዛኛው የእርስ በርስም ሆነ ከውጭ ጠላት ጋር ይደረጉ የነበሩ ውጊያዎች የሚከወኑት በጦር እና ጎራዴ በሚደረግ የጨበጣ ውጊያ ነው፡፡ የጨበጣ ውጊያን በድል ለማጠናቀቅ ደግሞ ፈረስ ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ የአድዋ ጦርነት በፈረስ አጋዥነት ለድል እንደበቃ ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ ለ‹‹ባንዳ እርግማን›› አፋችን የሾለውን ያህል ‹‹ፈረሶችን›› አመስግነናቸው አናውቅም፡፡ ለኢትዮጵያ ነፃነት ከ ‹‹ባንዳዎች›› እና ‹‹ከፈሪዎች›› ይልቅ ፈረስ የነበረው አስተዋፅኦ ታላቅ ነው፡፡ ፈረስ ለቀደሙ ነገስታት ባለውለታ፣ የህይወታቸው አለኝታ ነበር፡፡ ለዚህም ይመስላል ብዙ ነገስታት ከ አባታቸው ይልቅ የፈረሳቸው ስም ጎልቶ የሚወጣው፡፡ ለምሳሌ የአፄ ቴወድሮስን ብናነሳ፡
‹‹ታጠቅ ብሎ ፈረስ፣ ካሳ ብሎ ስም
አርብ አርብ ይሸበራል፣ ኢየሩሳሌም››……ተብሎ ተገጥሞላቸዋል፡፡









