Wednesday, May 6, 2015

ኮሎኔል አብዲሳ አጋ

ኮሎኔል አብዲሳ አጋ የተወለደው በ፲፱፻፲፪(1912) . በኦሮሚያ ክልል፣ ወለጋ ዞን ነበር። በ፲፪(12) ዓመቱ አባቱ በንዴት ወንድማቸውን በመግደላቸው ሲታሰሩ አብዲሳ አባቱን ለማስፈታት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ቢያደርግም ሳይሳካ በሞት ተቀጥተዋል። በኋላም በ፲፬(14)።፤ ዓመቱ የኢትዮጵያን ጦር በመቀላቀል ሀገሩን ማገልገል ጀመረ። አብዲሳ ጦሩን ከተቀላቀለ ከሁለት አመት በኋላ አድዋ ሽንፈት ለመበቀል የዛተው ፋሺስት ሙሶሎኒ በድጋሚ ኢትዮጵያን ሲወር ሀገሩን ለመከላከል በ፲፮(16) ዓመቱ ወራሪውን ጦር መዋጋት ጀመረ። ውጊያ ላይ ባጋጠመው የመቁሰል አደጋ ህክምና ላይ ከቆየ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ፒያሳ አካባቢ በሚገኝ ቤት በቁም እስር ላይ ነበር። በኋላ ጣልያን ኢትዮጲያን እንዲያስተዳድር በሾመችው ግራዚያኒ ላይ የመግደል ሙከራ ከተደረገ በኋላ አብዲሳ አጋ እና ሌሎች 37 የሚሆኑ የቁም እስረኞች ተጠርጣሪ ተብለው በከባድ ስቃይ እስር ቤት ከቆዩ በኋላ በወቅቱ የጣልያን ግዛት በነበረችው በሶማሊያ በኩል ወደ ጣልያን ተወስዶ በሲሲሊ ደሴት በሚገኝ እስር ቤት እስረኛ ተደረገ።

አልሸነፍ ባይነት መለያው የሆነው አብዲሳ እስር ቤት እያለ ጁሊዮ ከሚባል ዮጎዛላቪያዊ ጋር ተዋዉቆ ጓደኛ ይሆናሉ፤ ሁለቱ ተማክረዉ የተወሰኑ እስረኞችን ይዘዉ ጫካ ገቡ፤ ከጥቂት ቀናት በኋላ ተመልሰዉ መጥተዉ ጠባቂ ፓሊሶችን አፍነዉ ገለዉ ልብሳቸዉንና እስረኞችን አስለቅቀዉና ዘርፈዉ ወደ ጫካ ይመለሳሉ። ጫካ የገቡት እስረኞች ተደራጅተዉ ወጣቱን አብዲሳ አጋን የጎበዝ አለቃ አድርገዉ መርጠዉ ከጣሊያን ጦር ጋር ይዋጉ ጀመር፤ ለጣልያን ጦርም ራስ ምታት ሆነዉባቸዉ ነበር፤ ጦርነቱ እየገፋ ሲሄድ የተባበሩት ሀይላት አሜሪካ፣ እንግሊዝ ራሽያና ፈረንሳይ እነ አብዲሳና ጁሊዮን እዉቅና ሰጥተዉ ጣሊያን ሲዳከም መጀመሪያ ሮም የገባዉ ወጣቱ አብዲሳ አጋ ነበር፤ ሮም ሲገባም የኢትዮጵያን ባንዲራ እያዉለበለበ ነበር፤ ከዛም እንግሊዝ የወታደራዊ ፓሊስ አዛዥ አድርጎ ሾሞ ወደ ጀርመን ልኮት ከናዚ ጋር ባደረገዉ ጦርነት ታላቅ ጀብዱ ፈፅሟል።ጦርነቱ ካከተመ በኋላም እነዚሁ ሀገራት ከነሱ ጋር እንዲቆይ ስልጣንም እንደሚሰጡት ጠይቀዉት ነበር፤ ወጣቱ አብዲሳ ግን ሀገሬ ድሀ ነች ነገር ግን ሀገሬና መንግስቴ ናፍቀዉኛልና ሀገሬ እገባለሁ ብሎ ወደ ሀገሩ መጣ።

በሻለቅነት ማዕረግ የእንግሊዝ ጦር አዛዥ የነበረው የበረሀ ተኩላዉ አብዲሳ አጋ በጣልያንና በጀርመን በረሀዎች ስንት ጀብዱ የፈፀመ ጀግና ኢትዮጵያ ሲመጣ ኃይለስላሴ እራሳቸዉ ተቀብለዉ ወደ መከላከያ ሚንስትሩ ራስ አበበ አረጋይ ላኩት፤ ራስ አበበ አረጋይና ዙሪያቸዉ ያሉት ባለስልጣኖች ሻለቃ አብዲሳ አጋን የሚገባዉን ክብርና ማዕረግ እንደመስጠት ለካዴትነት ወደ ሆለታ ጦር አካዳሚ ላኩት፤ ለኮለኔልነት ማዕረግ እንኳ የበቃዉ በማርሻል ቲቶ ጉብኝት ምክንያት ነበር፤ ማርሻል ቲቶ ጀኔራል አብዲሳ የታለ ብሎ በመጠየቁና ቀዳማዊ ኃይለስላሴን በማስታወሱ አጼ ኃይለስላሴ የኮሎኔልነት ማዕረግ ሰጥተዉ የክብር ዘበኛ አድርገዉ ሾመዉት ነበር።

ኮሎኔል አብዲሳ አጋ ኢትዮጵያን ለአለም ያስተዋወቀ፣ ባልተወለደበትና ባላደገበት ምድር ጠላትን ያስጨነቀ፣ ያሸበረ፤ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ወራሪዋ ሀገር ሮም ወስጥ ያዉለበለበ ጀግናችን ነበር።
                                      (ምንጭ: / ፍቅሬ ቶሎሳ "አብዲሳ አጋ")

              "ዘላለማዊ ክብር ለሀገር ላዊነት ለተሰው አርበኞች!"

ለ በለጠ መረጃ:

No comments:

Post a Comment