Friday, January 15, 2016

+ የዘገየህ ምነው?+

እስራኤል ዘነፍስን~ ከኃጥያቱ ቀንበር
እስራኤል ዘስጋን~ ምድር ቸነፈር
ያዳንሃቸው መሲዕ~አንተ ብላቴና 
እኛንም አድነን~እባክህ ቶሎ
አየህ ብላቴናው፡
ሰማይ ተለጉሞ
ምድር ሆዷ ታሞ
በደረቀ ማሳ~በደረቀ ተስፋ
ወይፈን~ተኝቶ ቀኑን እየገፋ
ምነው ምን በደልንህ~ድምፅህ ሁሉ ጠፋ
…………
አየህ ብላቴናው፡
የረሃብ ሰቀቀኑ 
የችግር ዲደኑ
አብሮን ቢራመድም~እኩል ከዘመኑ
አራሽ ገበሬ ግን~አልተወም መጥመዱን
በደከመ በሬ~በደከመ ወይፈን፤
…..
እኒያም ምስኪን በሬዎች፡ 
ሳይፈቅዱ ተወልደው
ሳይወዱ ተጠምደው
ከማሳው ተኝተው~ይኸው ስራ ፈቱ
የሚላስ ልመና~ወደ አንተ ቃተቱ
……..
እንዲህ እየሆነ 
እንዲያም እየሆነ 
የትናንት ማንነት እየመነመነ
በሬዎች ደከሙ~ቀንበሩ ከበደ 
በኮሩ መሳሳት~ጫንቃቸው ነደደ
በገራፊው ጉልበት~ጀርባቸው ተላጠ
በመንበርከክ ብዛት~እግራቸው ጎበጠ
…..
እናም አንተ መሲህ
ስማን ከወዴት ነህ?
እንዴት ዝም ትላለህ? 
ይሄን ሁሉ እያህ፤
የዘገየህ ምነው?
አራሹን ተው በለው~ወይ በሬውን ፍታው
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
[ዘላለም☞የእናቱ ልጅ]; January 14, 2016


2 comments:

  1. በገራፊው ጉልበት~ጀርባቸው ተላጠ
    በመንበርከክ ብዛት~እግራቸው ጎበጠ

    ReplyDelete
  2. አራሹን ተው በለው~ወይ በሬውን ፍታው

    ReplyDelete