Wednesday, August 31, 2016

"ሪፖርት ላይ ይፀድቃል..."

ደበበ ሰይፉ "መሣቅ እኮ ይቻላል...አለማልቀስ ነው ጭንቁ" እንዳለው አንዳንዴ "ለበጣም" ሆነ "ገበጣ" ሳቅን ውስጥ ገፍቶ ማውጣት ለጤና ጥሩ እንደሆነ አንዳንድ ስቀው የማያውቁ ሐኪሞች ይመክራሉ፡፡
እስኪ እኛም እንገልፍጥ፡
ከላይ ወደ አነሳሁት ርዕስ ጉዳይ ስመለስ..... ዛሬ አንድ ጓደኛዬ የነገረኝን ቀልድ መሠል እውነት ጀባ ልበላችሁ፡፡
ልማታዊ የሆኑ ወጣቶች ለአረንጓዴ ልማት አብዮቱ ንቅናቄ ችግኝ እየተከሉ ነው ( አብዮት የምትለዋ ቃል ለዘብ ባለ ልማታዊ ቃና ትነበብልኝ)፡፡
...... ቃና ስል ምን ትዝ አለኝ መሠላችሁ፡፡ ሰሞኑን እንደፈረደብኝ የተከራየሁት ቤት ሊሸጥ ስለሆነ ቤት እየፈለግሁ ነው፡፡ ዛዲያ እላችሁ አንዲት ፅሁፍ ላይ "ሽማግሌ" በንግግር
ላይ ግን የኮረዳነት ስሜት የሚቃጣቸው ሰትዯ የቤቱን ዋጋ ከነገሩኝ በኋላ.....ምን ቢሉኝ ጥሩ ነው፡፡ 
"........የማይረብሽ፣ የማያመሽ፣ የማይጠጣ....ሶሪ ቤትክ አምጠህ መጠጣት ግን ትችላለህ፤ እንዲሁም ቺክ የማያመጣ ተከራይ ውስጤ ነው" አሉኝ፡፡ ......እኔም ወደ ውስጥ ሳያስገቡኝ ግቢውን ለቅቄ እብስ፡፡
ወደ ቀደመ ነገሬ ስመለስ ልማታዊ ወጣቶች ችግኝ ተካፍለው የተለያየ ጉድጓድ ላይ እየተከሉ ነው (........ በነገራችን ላይ እኔም ልማታዊ ተካይ ነበርሁ፡፡ ያኔ በልጅነቴ ብዙ ዛፎች ተክዬ ነበር፡፡ .......ምን ዋጋ አለው፣ አባቴ ጥፋት ባጠፋሁ ቁጥር ለመግረፊያ ቆርጦ ጨረሳቸው፡፡ ......አባቴ ለጀርባዬ ንቅሳትና ኦዞን መሣሣት ምክንያት መሆኑን ሳስብ እምባዬ ጎርፍ ሆኖ አንዳንድ አዲስ አበባ ነዋሪዎችን ከማፈናቀሉ በፊት በሶፍት የማያዳግም ወታደራዊ እርምጃ ወሰደሁበት፡፡ ...... አባቴን ሐጢያት ለማቅለል ብዬ ባለፈው ሐምሌ 20 በላይ ችግኞች ተክያለሁ_የት እንዳሉ ግን አይቻቸው አላውቅም፡፡ ምን አልባት አንዳንድ.....አይ ይሄ ነገር በዛ መሠለኝ.....ጥቂት ፀረ ልማት ኃይሎች ነቅለዋቸው ይሆናል)
ወደ ልጆች ስንመለስ....አንደኛው ልጅ በትክክል ተክሎ ጨርሶ የሌላኛውን ልጅ ሲመለከት አትክልቶቹን ገልብጦ ተክሏቸዋል ( ....ምን አልባት ጥናቱን ቀድሞ አውቆ ሉሲ እየተበቀለላት ይሆን?.....አይ እኛ!..... ሉሲ ያነስን ትውልዶች!)
"አንተ ለምን ገልብጠህ ተከልከው....አይፀድቅም እኮ.... ያምሃል እንዴ! ቅርንጫፍ ተገልብጦ ይተከላል?" ሲል ጓደኛው ጭቃ እንደያዘው መኪና አጓራበት፡፡
አጅሬው ምን ብሎ መለሰ መሠላችሁ፡
"ችግር የለም... ሪፖርት ላይ ይፀድቃል" አለው አሉ፡፡
እህ እህ.... "ይች ናት" አለ አበባው መላኩ፡
"ይች ናት
ይች ናት
ሀበሻ የቅኔ ምታት
ለሰው እሰወር ብሎ
..........
ለራስም አለመፈታት!"
........................................


1 comment: