Monday, November 27, 2017

‹‹አንድም እናት በወሊድ ምክንያት…..››

-----------------------------------
‹‹
ሌሊት ላይ ታመመች
ምጤ መጣ ብላ፣ ሆስፒታል ውስጥ ገባች
አማጠች አማጠች
ሌሊቱ ጎህ ሳይቀድ፣ ሞት ተገላገለች፤
ሁሉም ሰው አዘነ፣ ዘመድ አለቀሰ
ሁለት ነፍስ፣ በአንድ ጉድጓድ፣ ቀብሮ ተመለሰ››
በቃ!

--------------------------------------------
ይህ ዜና በጓደኛዬ እህት ደርሶ ሐዘኑ ምን ያህል ልብ ሰባሪ መሆኑን በአይኔ ልመልከት እንጂ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ቅስም ለዘመናት ሲሰብር የኖረ ሰቆቃ ነው፡፡ የነፍሰጡር ሞት አንድ ሞት አይደለም፣ የብዙ ሞቶች ጥርቅም ነው፡፡

ምንም እንኳን የዘመናዊ ህክምና መስፋፋት ‹‹የልምድ አዋላጆች›› ልፋትና ጉድለት እየተካ መምጣቱ ደስ የሚያሰኝ ቢሆንም፣ እየታየ ያለው ሙያዊ ቸልተኝነትና የብቃት ማነስ አሁንም የብዙዎችን አንጀት ማንሰፍሰፉ፣ የቤተዘመድን ቅስም ማርገፉ አልቀረም፡፡
ኢትዮጵያ ‹‹አንድም እናት በወሊድ ምክንያት መሞት የለባትም›› በሚለው መፈክሯ ብዙ ርቀት የተጓዘች፣ የምዕተ ዓመቱን ግብም ለማሳካት ብዙ ጥረት ያደረገች አገር መሆኗ የሚካድ ባይሆንም ተከታታይነቱን ማስቀጠል ላይ ግን ዳገት የሆነባት ይመስለኛል፡፡ በተለይ በተለይ በማህበረሰቡ ዘነድ ባለው ባህላዊ እሴት እና የመሰረተ ልማት ችግር ምክንያት ክትትል የሚያደርጉና በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶች ቁጥር አሁንም ዝቅተኛ ነው፡፡
የጤና ጥበቃ 2009 . ጥቅል ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሆነ ያረግዛሉ ተብለው ከተገመቱት 3.17 ሚሊዮን እናቶች መካከል 71% ያህሉ በሰለጠነ ባለሙያ ወልደዋል ይላል፡፡ በግለሰቦች የሚሰሩ ጥናቶች ደግሞ ከዚህ በጣም ያነሰ ቁጥር ያሳያሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ችግሩ ከከተማ ይልቅ ገጠር ላይ ይከፋል፡፡
ዛሬ የሞተችዋ እንስት ዓመታት በፊት ከተማ ወደሚገኘው ጤና ተቋም ሳደርስ በአሳዛኝ ሁኔታ በምጥ ገጠር ውስጥ ህይወቷ ያለፈውን ዘመዴን አሳሰበኝና አለቀስኩ፡፡ በየአመቱ ከአቅም በላይ በሆነ ሁኔታም ይሁን በቸልተኝነት የማህፀናቸውን ፍሬ ሳይገላገሉ ወይም ተገላግለው ለሚያሸልቡ እናቶች ሁሉ አለቀስኩ፡፡ እምባ ለነገ እንስቶች ፈውስ ይሆን ይመስል አለቀስኩ፡፡
እናት ደረቷን እየመታች ልጇንና በማህፀን የቀረ የልጅ ልጇን ስትቀብር እያየሁ እንዴት አላለቅስ??? ምን አንጀተ-ደንዳን ሰው ቢሆን የነፍሰጡር ሞትን አይቶ የማን አንጀት ይችላል??? 
የኢትዮጵያ የጤናና ዲሞግራፊክ ጥናት .. 2016 . ባወጣው ሪፖርት መሰረት 100,000 እናቶች መካከል 412 የሚሆኑት በወሊድ ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡ ይህ ከላይ ባስቀመጥነው የነፍሰጡሮች ቁጥር ሲሰላ፣ ኢትዮጵያ በዓመት 13,000 በላይ እናቶችን በወሊድ ምክንያት ታጣለች፡፡

በመጨረሻም አጭር መልዕክት አስተላልፌ ዞር ልበል፡፡
ነፍሰጡር ሴትን መንከባከብ ሀገርን መንከባከብ ነው፡፡ በነፍሰጡር እናቶች ማህፀን ውስጥ የነገ ሀገር አለች፡፡ በነፍሰጡር ሴት ነፍስ ውስጥ ብዙ ነፍሶች አሉ፡፡ ብዙ ተስፋዎች አሉ፡፡ ልክ በዛሬዋ ሟች ነፍስ ውስጥ 3 ዓመት ልጇ ተስፋ፣ የባሏ እጣ ፈንታ፣ የእናቷና የቤተሰቦቿ ህልም አብሮ እንደተቀበረው፡፡ ችግሩን ቀለል አደረግሁት እንጂ ከዚህም ይብሳል፡፡ ነፍሰጡር ሴትን መንከባከብ የባለሙያዎችና የቤተሰብ ሃላፊነት ብቻ አይደለም፣ ሁሉንም ማህበረሰብ ይመለከታል፡፡ ‹‹አይመችሽም ሌላ ታክሲ ጠብቂ›› ከሚለው የታክሲ ረዳት ጀምሮ ክትትል እስከሚያደርገው የጤና ባለሙያው ድረስ ያለው ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ነፍሰጡር ሴቶችን የመንከባከብና የማገዝ ሞራላዊ ግዴታ አለበት፡፡
‹‹ ፈጣሪ ሆይ ብትፈቅድስ አንድም እናት በወሊድ ምክንያት አትሙት!››
አሜን!



No comments:

Post a Comment