Sunday, June 21, 2015

የአስመሳዮች ዘመን

                   አስመሳይ ካልሆንህ አታንበው? ከጀመርኸው ጨርሰው!
አንድ ታሪክ ልንገራችሁ፡፡ እውነተኛ ታሪክ፡፡ በአንድ ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚገኙ ገዳማት ወደ አንዱ ብቅ ብየ ነበር፡፡ አንድ አባት የማግኘት ዕድሉ ገጥሞኝ ነበር፡፡ አባ ገ/ሕይወት ይባላሉ፡፡ በመንፈስ የበቁ፣ ለፀሎት የነቁ አባት፡፡ አባ አንድ ታሪክ ነገሩኝ፡፡ መግቢያውን ላለማገመድ ወደ ታሪኩ ልጋባ፡፡ አባ እንዲህ ሲሉ ጀመሩ፡፡
“አንድ ደግ ገበሬ ነበረ፡፡ እንደ ደጉ አብርሃም እንግዳ ተቀባይ ነበር፡፡ እንግዳ ይቀበላል፣ ያበላል፣ ያጠጣል፣ ያሳድራል፣ መንገድ አሳይቶ ይሸኛል፡፡ አንድ ቀን ግን ያልተጠበቀ ነገር ገጠመው፡፡ እንደተለመደው ሶስት ወጣቶች ከሩቅ ሀገር እንደመጡ ለዚህ ደግ ገበሬ አስረድተው “ የእግዜር እንግዳ” ነን አሳድሩን ሲሉ ተማጠኑ፡፡ "  አባ ድምፃቸውን ጠራርገው ትረካቸውን ቀጠሉ፡፡

".....ሁሌም ድሃንና እንግዳን በማብላትና በመርዳት የሚታወቁት ደጉ ገበሬ በደስታ ተቀብለው ወደ ቤት አስገቧቸው፡፡ ውሃ አስሙቀው እግራቸውን አጠቧቸው፡፡ ቡና አፈሉላቸው፣ ጠጅ አጠጡአቸው፣ ሸኸር በግ አረዱላቸው፡፡ እየተጫወቱ እሰከ ምሽቱ አምስት ሰዓት ቆዩ፡፡ ከዚያም ቀጣዩ ጊዜ ወደምኝታ ሆነ፡፡ ደጉ ገበሬና ባለቤታቸው አልጋቸውን ለእንግዶች አስረክበው መሬት ተኙ፡፡ የሌሊት ብርድ ልብሳቸውን ለእንግዶች ሰጡ፡፡ እንግዶች ግን ብዙ አልተኙም ወዲያውኑ ከሌሊቱ 6 ሰዓት ተነሱ፡፡ ወደ ሀገራቸው ለመሄድ አይደለም፡፡ መጀመሪያ የያዙትን ባትሪ አበሩ፡፡ እርስ በእርሳቸው ይከራከራሉ፡፡ በፍጥትነት ተነስተው በያዙት ቢላዋ እያንገራገሩ ቤተሰቡን ባገኙት ገመድ የፍጥኝ ማሰር ጀመሩ፡፡ አንደኛው ወጣት በተግባራቸው መስማማት ስላልቻለ ሁለቱ ወጣቶች የአንደኛውን ወጣት አንገት በቢላዋ ቀረጠፉት፡፡ ቤተሰቡ በፍራቻ ተዋጠ፡፡ ልጀ እነዚያ ሽፍቶች በእግዜር ስም የሚለምኑ አስመሳይ ሽፍቶች ነበሩ፡፡ በማሰርና በማንገራገር አላቆሙም፣ ባለቤቶችን እየገረፉ ያስቀመጡትን ንብረት መጠየቅ ጀመሩ፡፡ ሴት ልጆቻቸውን ደፈሩ፡፡ ቤት ውስጥ የነበረውን ወርቅ፣ ብርና ውድ ዕቃ ሁሉ ዘረፉ፡፡ ከዚያም በቢላዋ የቀረጠፉትን ጓደኛቸውን እንዲሄዱ ሲጠይቁት አልሄድም አለ፡፡ ከምንገልህ አብረኸን መሄድ ይሻልሃል አሉት፡፡ ሳይወድ በግድ ተስማማና ቤቱን ለቀው ከአካባቢው ተሰወሩ፡፡አየህ ልጀ ከዚያ በኋላ የአካባቢው ሰው እንግዳ መቀበል አቆመ፡፡”

አባ ታሪኩን ተርከው ሲጨርሱ ፊታቸውን ኮስተር አድርገው አባታዊ በሆነ ፍቅር ወደኔ እየተመለከቱ እንዲህ አሉኝ፤ “አየህ ልጀ ይች ዓለም በሁለት ተቃራኒ ነገሮች የተሞላች ናት፡፡ ደግ-ክፉ፣ እውነት-ውሸት፣ ጨለማ-ብርሃን፣ ሀብታም-ድሃ፣ ፃድቅ-ኃጥዕ፣ ደስታ፣ኀዘን፣ ገዥ-ተገዥ፣ አለቃ-ጭፍራ፣ ብቻ ብዙ ናቸው፡፡ ልጀ ይህች ዓለም ጥሩና የተሻለች ልትሆን የምትችለው ሁለቱን ለማሰታረቅ በምናደርገው ጥረት ነው፡፡ ከመልካሙ ነገር ይልቅ መጥፎው ከበለጠ ይህች ዓለም ትጠፋለች፡፡ ጦርነት፣ ረሃብ፣ ቸነፈር፣ ማህበራው ቀውስ ይስፋፋል፡፡ ዓለም የተሻለች እንድትሆን መልካሙ ነገር ተሽሎ መገኘት አለበት፡፡ አሁን ልጀ ዘመኑ ከብዷል፡፡ ዘመኑ የአስመሳዮች ነው፡፡……” አባ ትንሽ ዝም እንደ ማለት ብለው ሽቅብ ወደ ተራራው ጫፍ እየተመለከቱ ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡

“……..በጠራራ ፀሐይ የሰሩትን ስህተት ስትነግራቸው አይናቸውን በጨው አጥበው የአምስት ፃድቃን ስም እያነሱ ይምሉልሃል፡፡ የሰው ልጅ ከህሊናውና ከአምላኩ የተጣለበት ከባድ ዘመን፡፡ ፍቅርና ሰላም እንደ ጥቅምት ቁር የቀዘቀዙበት ዘመን፡፡ ልጀ ነብዩ በመፅሐፍ “ፅድቃችን የመርገም ሆነ” እንዳለው፤ ፅድቃችን የታይታ፣ ኑሮአችን የአስመሳይነት፣ ቃላችን የውሸት፣ ስራችን ለይምሰል ሆነ፡፡ አስመሳዮች በእውነተኞች ወንበር ተቀመጡ፣ እውነት መናገር የሚያሰቀጣ፣ መልካም ማሰብ የሚያስቀጣ፣ ጥሩ መስራት የሚያስነቅፍ እየሆነ መጣ፡፡ ልጀ እኔ ዘመኔን ጨርሻለሁ፡፡ መጪው ያንተ ዘመን ግን ከባድ ነው፡፡ የአስመሳዮች ዘመን ነው፡፡ በአስመሳዮች ክፉ ስራ ሰው ሁሉ ክፉ የሚሆንበት ዘመን፡፡ እንደ ሽፍቶቹ ስታጎርስ የምትነከስበት ዘመን፡፡ እንደ ሽፍቶቹ በሌሊት ሳይሆን በጠራራ ፀሀይ አስመሳዮች የሚዘርፉበት ዘመን፡፡ አዎ ልጀ አውነትን መናገር፣ ለህሊና መኖር፣ የፈጣሪን ትዕዛዝ ማክበር ዋጋ የሚያስከፍሉበት ዘመን፡፡ ደህናውን ከአስመሳዩ መለየት የሚከብድበት ዘመን፡፡ ልጀ አንተ ግን ከአስመሳዮች ተለይ፡፡ ለህሊናቸውና ለአምላካቸው ሳይሆን ለሆዳቸውና ለማንነታቸው ከሚጨነቁ፣ ለእውነት ጠላት ከሆኑ አስመሳዮችና አድር-ባዮች ተጠንቀቅ፡፡ ልጀ መሬት ለሚበላው ስጋህና ማንነትህ ብለህ በአድርባነት ከምትኖር ይልቅ ስለሃቅና ስለ እውነት ብለህ ተገፍተህ ብትኖር ለህሊናህ ሰላምን ለነፍስህ እረፍትን ታገኛለህ፡፡ በመጭው ዘመን ትውልድም በመልካም የመታሰብ እድል ይኖርሃል፡፡”  አሉኝና አደራ በሚመስል መልኩ በአባታዊ ፍቅር በግራ አጃቸው ፀጉሬን እያሻሹ በቀኝ እጃቸው ደግሞ ከቀለባቸው እፍኝ ሽንብራ ዘግነው ሰጡኝና በሰላም አገርህ ግባ ብለው አሰናበቱኝ፡፡ 

ያኔ ልጅነቴ ነው መሰል ብዙ ነገሮች አልገቡኝም፡፡ አሁን ገባኝ፡፡ ይህን ስፅፍ ከአባ ጋር ያለሁ ያህል አንዳች የደስታ ስሜት ይነዝረኛል፡፡ አብረውኝ የተቀመጡ ያህል ይሰማኛል፡፡ አባን አሁኑኑ ማግኘት አሰኘኝ ግን አልችልም፡፡ በህይወት ስለመኖራቸውም እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በህይወት አለመኖራቸውን ሳስብ ውስጤ ይጨነቃል፡፡ እያስመሰሉ ሳይሆን እየኖሩ የሚያስተምሩ፣ እያነበቡ ሳይሆን እየተገበሩ የሚሰብኩ፣ እየሰሙ ሳሆን እያዩ የሚናገሩ፤ አባን አይነት ሰዎች ናፈቁኝ፡፡ አሁንም ውስጤ ይጨነቃል፡፡ አባ የት ነዎት? አባ ባይኖሩም መንፈሳቸው ህያው ነው፡፡ ቃላቸውም እውነት ነው፡፡ አዎ ይሄ የኔ ዘመን ነው፤ ያኔ አባ የነገሩኝ የተኩላዎች ዘመን፡፡ የበግ ለምድ የለበሱ አስመሳይ ተኩላዎች ዘመን፡፡ የእኔና የመሰሎቸ የማስመሰል ዘመን፡፡ በውሸት ምሁር፣ በማጭበርበር ሀብታም፣ በማስመስል ባለስልጣን፣ በመናገር ደጅአዝማች፣ በመለፍልፍ ነብይ፣ በመናገር ፃድቅ የሚሆንበት የማስመሰል ዘመን፡፡ አስመሳዮቹን እንተዋቸውና እኔ እና አናንተ የት ነን? በድሆች ስም አላጭበረበርንም፣ በውሸት የዲግሪ ባለቤት አልሆንም፣ በጉቦ ሃብታምና ባለስልጣን አልሆነም፣ በውሸት አልመሰከርንም፣ በሌሎች ስም አልከበርንም፣…….ቤት ይቁጠረው፡፡ የአስመሳዮች ዘመን መች ይሆን የሚያበቃው፡፡ በሐይማኖት፣ በዘር፣ በጎሳ፣ በቀለም፣ በዘር፣ በቋንቋ፣ በአነጋገር፣ በአስተሳሰብ የሚያስመስሉ  ሰዎች አድሜስ ስንት ነው? ዘመኑን ለእግዜሩ አንተወው፡፡ እኛ ግን ከአስመሳዮች እንለይ፣ ከማስመሰልም አንራቅ-ለህሊናችን ሰላምን ለነፍሳችን እረፍትን እናገኝ ዘንድ፡፡ እኛ አስመሳይ ስንሆን ነገ ልጆቻችን፣ ተማሪዎቻችን፣ ቤተሰባችን፣ ህዝባችን፣ አስመሳይ ይሆናል፡፡ ደግነት፣ ፍቅር፣ ሰላምና ተስፋ ቦታ ያጣሉ፡፡ ከአስመሳይነት ስንወጣ ግን ሌላ ደግ ሰው እናፈራለን፤ ከዚያም ትንሾች መቶ፣ ሺ፣ሚሊዮን እንሆናለን፡፡ ከዚያም የዓለም ያስመሳይነት ዘመን ያበቃል፡፡ መቼ? ይህን ታላቁ መፅሃፍ እንዳለው፣ ባለቅኔው እንደዘረፈው፣ ከያኒው እንዳዜመው  ጊዜ ለኩሉ ብለን እንለፍ፡፡
ጊዜ ለኩሉ!
ሻሎም!

ሰኔ 14፣ 2007 ዓ.ም-ሸገር

3 comments:

  1. ልጀ መሬት ለሚበላው ስጋህና ማንነትህ ብለህ በአድርባነት ከምትኖር ይልቅ ስለሃቅና ስለ እውነት ብለህ ተገፍተህ ብትኖር ለህሊናህ ሰላምን ለነፍስህ እረፍትን ታገኛለህ፡፡ በመጭው ዘመን ትውልድም በመልካም የመታሰብ እድል ይኖርሃል፡፡”

    ReplyDelete
  2. “አየህ ልጀ ይች ዓለም በሁለት ተቃራኒ ነገሮች የተሞላች ናት፡፡ ደግ-ክፉ፣ እውነት-ውሸት፣ ጨለማ-ብርሃን፣ ሀብታም-ድሃ፣ ፃድቅ-ኃጥዕ፣ ደስታ፣ኀዘን፣ ገዥ-ተገዥ፣ አለቃ-ጭፍራ፣ ብቻ ብዙ ናቸው፡፡ ልጀ ይህች ዓለም ጥሩና የተሻለች ልትሆን የምትችለው ሁለቱን ለማሰታረቅ በምናደርገው ጥረት ነው፡፡

    ReplyDelete
  3. ከዚያም የዓለም ያስመሳይነት ዘመን ያበቃል፡፡ መቼ? ይህን ታላቁ መፅሃፍ እንዳለው፣ ባለቅኔው እንደዘረፈው፣ ከያኒው እንዳዜመው ጊዜ ለኩሉ ብለን እንለፍ፡፡

    ReplyDelete