Saturday, May 7, 2016

"ከ ምስራቅ ሰማይ ስር_ክፍል 1…"

ሰኞ ጥዋት 12 ሰዓት-ከፋሲካ ማግስት፡፡ ጦር ሃይሎችና ወይራ ሰፈር የተምታታበት ሹፌር እንደምንም ከያለንበት ለቃቅሞ ከጥዋቱ አንድ ሰዓት አዲስ አበባን የኋሊት ትቶ ወደ ወደ ምስራቅ ተምዘገዘገ፡፡ ከዚያም የፍጥነት መንገዱን 120 ረግጦ መሪውን ወደ ምስራቅ ወደረ፡፡ ናዝሬትን በግራ አይናችን ሾፈናት በፈጣን መንገዱ በቀኝ በኩል አለፍናት፡፡ የወንጂ ሸንኮራ አገዳ ማሳ ከሩቅ ለዓይን ያሳሳል፡፡ ለአፍታ አቁመን መተሃራ ከተማ ቡና ቀመስን፡፡ የከረዩዎች ሰፈር በደራሽ ዝናብ በመጣ ጎርፍ ተጥለቅልቋል፡፡ በጥዋቱ የደነበረው ሹፌራችን አዋሽ መዳረሻ አንዲት ምስኪን እርግብ እስከወዲያኛው አሰናበተ፡፡
ከሜጫ ታራሮች ተነስቶ በዝምታ ወደ ምስራቅ የሚያዘግመውን የአዋሽ ወንዝ በዘመዶቻችን ቻይናዎች በተሰራው አዲስ ድልድይ ቆርጠነው አለፍን፡፡ አፍታ የሎሬት ፀጋዬ /መድህንን አዋሽ የተሰኘ ግጥም በውስጤ ማነብነብ ጀመርሁ፡፡
"አስከመቼ ይሆን አዋሽ? 
አዋሽ
የሜጫ ስር ፍሳሽ
አዋሽ ህመምህ ምንድን ነው?
ህመምህስ አንተስ ምንድን ነህ
?
...................

...................."
አዋሽ 95 . ርቃ ከምትገኘው ጭሮ (አሰበ ተፈሪ) ከተማ ምሳ ለመብላት ሹፌራችን እኛን እንደ ኳስ እያነጠረ ወጣ ገባውን መንገድ ይምዘገዘጋል፡፡ በጎናችን የጥንቱ የባቡር መንገድ ዘንዶ መስሎ ተኝቷል፡፡ የባቡሩ መንገድ የጥንቷን የኮንትሮባንድ መናኸሪያ መይሶንን በመሃል ሰንጥቋት ያልፋል፡፡ አዲሱ የባቡር መንገድ ደግሞ ወጣ ብሎ በድልድይ ያልፋታል፡፡ በአርግጥ መይሶን አንደ ጥንታዊነቷ አይደለችም (በመኖርና ባለመኖር መካከል ያለች ከተማ ናት)፡፡

አሰበ ተፈሪ ደረስን፡፡ ምንም አንኳ ከተማዋ ታዳጊ ብትሆንም ምስቅልቅል ያለች ናት፡፡ ሹፌራችን እነ ሀመልማል አባተን ቤት ላሳይህ አለኝ፡፡ ምን ያደርግልኛል ይልቅ የሚበላ ነገር አሳየኝ አለኩት ቆጣ ብዬ፡፡ ሰው በደቦ የበሬ ስጋ እየመተረ፣ በደቦ ይጠጣል፡፡ ብቻ አበላላቸውና መጠጣቸው በጣም ያስፈራል (ግዳይ የጣለ አውሬ መስለው ታዩኝ)፡፡ ጎን ለጎን ደግሞ ጥጉን ይዘው ጫት የሚበሉ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ እርግጥ ከመጠጥ ቤቱ ይልቅ ጫት ገባያው ይደምቃል፡፡ ጥሩ ምግብ ቤት አጣን፡፡ አንድ የፍየል ጥብስ ቤት ተጠቆምንና ገባን፡፡ ጥብሱ በቃሪያ ሳይሆን በፍየሏ ፈርስ ተጠብሶ የመጣ ይመስላል፡፡ ምን አልባት ውሃውን ለጓሮ ጫት ማብቀያ ተቆጥቦ ይሆናል፡፡ ሸም በላንና ስፕራይት ጠጣንበት፡፡ ለራሳችን ሀበሻን ራሃብ እንጂ በሽታ አይገለውም፡፡ ጀርም ያለው ጀርመን ነው ምናምን ብለን አታለልነው፡፡ ለናሙና ያሰራነው ምግብ ጥሩ ስላልሆነ ሙዝ ገዝተን በተቋጠረልን ዳቦ እየገመጥን ወደ ፊት ተምዘገዘግን፡፡ አሰበ ሳልወጣ ግን አንድ ጥያቄ ልጠይቅ፡፡ አሰበ ተፈሪ ምን አልባ ስሟ ከጃሆይ ጋር የተያያዘ ይሆን? ምሳ ከቀመስንበት ቤት ቢራ ሲጠጡ ያየኋቸው ሰውዬ መልካቸው ቁርጥ ጃሆይን ይመስላሉ፡፡ በደንብ ላያቸው የጃንሆይ ትንሽ ወንድም ይመስላሉ፡፡ ልጠይቃቸው ነበር ግን የደቦው መጠጥ ውስጥ ስለሆኑ ሃሳቤን ቀየርሁ-የሚሆነው አይታወቅም፡፡
ከመይሶን ጀምሮ ሜዳ ላይ ምንም ነገር አይታይም-ከጫት ማሳ በቀር፡፡ እኔም በምናቤ ለትውልዴ እንዲህ ብዬ የእንጉርጉሮ ጥያቄ ጠየቅሁ፡

መይሶን ማዶ~ከጭሮ ሰማይ ስር
ደበሶና ሂርና~ ገለምሶ መንደር
ምድር ተወራለች~ አረንጓዴ እሳት~ አረንጓዴ ሐሩር
የበቆሎው እሸት~ሙዙ ወዴት ሄደ?
ማንጎ ብርቱካኑ~ወዴት ተሰደደ?
በምድር አሜካላ ትውልዴ ያበደ
?
………
ነገር ግን ጥያቄዬ እንደ ገደል ማሚቶ መልሶ ወደ ውስጤ ይጮሃል፡፡ መልስ አልባ ጥያቄ፡፡ ከራሴ ጋር በሃሳብ ስከራከር ከመኪናችን ፊት ላይ የሚል ድምፅ ከምናቤ መለሰኝ፡፡ 
…….
(
ዘላለምየእናቱ ልጅ)

No comments:

Post a Comment