Monday, May 16, 2016

"ከ ምስራቅ ሰማይ ስር_ክፍል 2..."

(አወዳይ፣ ባቢሌ፣ ካራማራ....)
መኪናችን ፊት ላይ የሚል ድምፅ ከምናቤ መለሰኝ፡፡ ሹፌራችን ተደናግጧል፡፡ በዚህ ቅፅበት አንድ ሚዳቋ መኪናችን በቀኝ በኩል ወጣ ስትሮጥ አየሁ፡፡ ሹፌራችን አንድ ጫት በልታ የመረቀነች ሚዳቋ ጋር ተጋጭቶ ነበር፡፡ እንደ እርግቧ እስከመጨረሻው አላሸለበችም፡፡ ህመሟን ዋጥ አድርጋ ወደ ጫካው ተምዘግዝጋ ገባች(ደግነቱ የዱር እንስሳ ጥበቃ በአካባቢያችን አልነበረም)፡፡ የሹፌሩን አነዳድ ሳየው የመረቀነ ይመስለኛል፡፡ ጫት ባይቅምም ጥብሷን የበላናት ፍየል በጫት ያደገች ስለሆነች በዚያ በኩል ደርሶታል፡፡ አሰበ እስከ ሀረር ድረስ በምርቃና አስፓልት ላይ እየዘለሉ የሚገቡ ፍየሎችንና ሰዎችን ማዬት የተለመደ ነው፡፡ ቀስ ብለህ ንዳ ልለው ብዬ መልሸ ዋጥሁት፡፡ በኋላ ግን  ዓይን ተነጋግረን አስተውሎ እንዲነዳ ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር አዋጠን ለገስነው፡፡

ጉዟችን ቀጥሏል፡፡ በጫት የተሞሉ ውብ መልካምድሮችን ለዓይናችን መመገቡን ቀጥለናል፡፡ የሂርናን ከተማ ዓይናችን ገርፈናት አለፈን፡፡ ቁልቢ ገብርኤልን ወደ ቀኝ ትተን፣ የድሬን መገንጠያ ወደ ግራን በጨረፍታ ተመልክተን ወደ አለማያ ገሰገስን፡፡ ቁልቢና ድሬን የመጎብኘት ፅኑ ፍላጎት ቢኖረንም፣ ጊዜው እየመሸ ነው፡፡ ወደ አሰብንበት ቦታ ደርሰን ማደር አለብን፡፡

ፀሐይ ከተራራ ላይ እንደተወረወረ ኳስ በፍጥነት ወደ ምዕራብ አድማስ መንከባለሏን ቀጥላለች፡፡ አንበሳው ዘዋሪያችን መሪውን ወድሮ ይዞ 500 . እዮቤልዩውን አክብሯል፡፡ አወዳይ ከተማ ደረስን፡፡ የኢትዮጵያው ኤክስፖርት ስታንዳርድ ጫት መፍለቂያ-አወዳይ፡፡ አወዳይ ያሉ ምርጥ ህንጻዎች የተገነቡት ለቢሮ ወይም ለሱፐርማርኬት አይደለም፡፡ ምን የመሰለ ህንፃ አገልግሎቱ የጫት መሸጫ ነው፡፡ አወዳይ ውስጥ መኪና ያልገዛ ጫት አብቃይ ገበሬ የለም እየተባሉ ይታማሉ፡፡ አወዳይ አፈሯ ወርቅ ባይኖረውም፣ በወርቅ የሚቀየር ጫት ማብቀል የቻለች መሬት ናት፡፡ ስለ አወዳይ ጫት ብዙ አስገራሚ እውነታዎችን የሰማሁ ቢሆንም፣ ለጊዜው ለሀገር ሳይሆን ለእኛ ደህንነት ሲባል በዚህ ይዛዘም፡፡ በሌላ ዘገባ እንገናኝ አለ………ቲቪ፡፡ አለማያ ደረስን፡፡ አለማያ ሐይቅ ነበር በሚባል መልኩ ለታሪክ የሚሆን የውሃ ምልክት ይታያል፡፡ አንጋፋውን የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲን አልፈን ሀረር ከተማ ገባን፡፡ ጀጎልን የማዬትም ሆነ የመጎብኘት እድል አልነበረንም፡፡ ሰዓቱ እየመሸ ስለሆነ፣ ጀጎልን በግራ ትተን ወደ ሶማሊ አዘገምን፡፡ ከተመለስሁ ሐረርና ድሬን እስከአፍንጫቸው የመጎብኘት ፅኑ ፍላጎት አለኝ ፡፡ የምስራቅ ፈርጦች....!

አሁን የኦሮሚያና ሶማሊ ድንበር አካባቢ ያሉትን የእግዜር ድንጋዮች እያየን ተመስጠናል፡፡ ደንጋዮቹ በተፈጥሮ ሰው አስተካክሎ የደራረባቸው ያህል ያስገርማሉ፡፡ ለዚህም ነው ሰው "እግዜር ድንጋዮች" እያለ የሚጠራቸው፡፡ 
ባቢሌ ከተማ ደረስን፡፡ ባቢሌ ወደ ኦሮሚያ አስተዳደር የዞረች ከተማ እንደሆነች ሰማሁ፡፡ በእርግጥ አስካሁን የከተማ እና የክልል ስም ቅይይር እንጅ በመሬቱ መካከል ያን ያክል የጎላ ልዩነት አላየሁም፡፡ ሠዓታትን ለፈጀው 300 . በላይ ለሆነው ጉዞዬ በግራም በቀኝም የምመለከተው አንድ ነገር ነው-በቆሎና ስንዴ እንደ ሰማይ የራቃቸው በጫት የተሞሉ ማሳዎችን፡፡ እነዚህ ማሳዎች ብቻ በበቆሎና በስንዴ ቢሞሉ ኑሮ ሀገሬ በስንዴ ልመና የነጭ ጉልበት ባልሳመች ነበር፡፡ ጫት ለሀገር ውድቀት እንጂ ዕድገት ያበረከተው አስተዋፅኦ ጎልቶ ይታየኝም፡፡ ቅር ያለው ካለ በርጫ ላይ ነው ማለት ነው፡፡
ሹፌራችን ሳይጨልም ለመድረስ ይመዘገዘጋል፡፡ እንደፈከረው አልቀረም፣ እነሆ ፀሐይ የምዕራብን አድማስ ሳትታከክ እኛ የካራማራን አፋፍ ተቆጣጠርን፡፡ ካራማራ ተራራ እንደ ስሙ ገኖ አልታየኝም፡፡ ያም ሆኖ ግን የካራማራን ተራራ አፋፍ ስመለከት አንዳች የነፃነት ስሜት ሰውነቴን ወረረኝ፡፡ የአድዋን ተራሮች ስመለከት የተሰማኝ ስሜት በድካም ከዛለ ሰውነት ሲወጣ ተሰማኝ፡፡
ካራማራ ካራማራ!
የሀገሬ ልጆች የጀግንነት ጎራ!
አፍታ የእናት አገር ጥሪ ሰለባዎች ውልብ አሉብኝ፡፡ የዚያድባሬ እሳት ያቃጠላቸው ምስኪን የሀገሬ ልጆች ከታራራው አፋፍ ስር በምናብ ታዩኝ! በእኔ እይታ ኮሌኔል መንግስቱ /ማርያም እንደ እቴጌ እጣይቱ ተመሳሳይ ጀብድ የፈፀመበት ታሪካዊ ተራራ ነው-ካራማራ! ታሪክ እራሱን የደገመበት ጀብድ? የምን ጀብድ???




…….


2 comments: