Wednesday, February 15, 2017

በ እንተ ቫላንታይን

(ለቀይ አምላኪዎች-ከ ዘይት ተራራ እስከ ቀይ ፓርቲ)


የተዘጋጃችሁ፣ ሩጫ የጀመራችሁ፣ በዝግጅት ላይ ያላችሁ፣ የተደናገራችሁና ግራ የገባችሁ…አንድ ቀኝ መላ ልንገራችሁ፡፡ በቅድሚያ ለቫላንታይን (ቅድመ ቃለ አመጣጥ=አማርኛ፤ ትርጉም=ባለን ታዬን……ዝርዝሩን በሌላ ጊዜ) ዋዜማ እንኳን አደረሳችሁ፡፡ ከ ደም ውጭ ቀይ የሆነ ነገር ለምሸጡ ሁሉ ይሄን ቀን እሺ ያድርግላችሁ፡፡ አሜን በሉ! (ሀሌ ሉያ እንዳትሉ!....ኢየሱስ ደም ሰጠ እንጂ ቀይ ልብስ አልሰጠም፣አልሸጠም)……

የአዲስ አበባ ህዝብ ከሰኞ እስከ አርብ ወጥሮ አዲስ አበባ ውስጥ ይሰራል፡፡ ቅዳሜና እሁድ ደግሞ ደብረ ዘይት ውስጥ ወጥሮ ይሰ’ራል! (ሳቅ)……………………………..(ይህ አረፍተነገር በደምና በወዝ የሚኖሩ ና ከስኳር በሽታ ነፃ የሆኑ የህዝብ አገልጋዮችን አያካትትም፡፡)

እሁድ 7 ሠዓት አካባቢ ደብረዘይት ስገባ፣ ከተማው ደብረዘይት ይሁን አዲስ አበባ ለመለየት ከብዶኝ ነበር፡፡ ሁሉም ሰው አዋጅ የተዋጀ ይመስል ጥንድ ጥንድ ሁኖ ደብረዘይትን ጥንድ የምትወልድ ከተማ አስመስሏታል፡፡
በዚህ ከቀጠለ ደብረዘይት ወደፊት የመስሪያ ሳይሆን የመሳረሪያ ከተማ ትሆናለች፡፡ ዩኔስኮ በክብር መዝገብ ሲያሰፍራት ኢቲቪ …..የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ውጤት ነው….. ብሎ የሚዘግብበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም፡፡ ከዚህ ትዝብቴ ስወጣ፣ ደብረዘይት ቀይ ነገር የሚበቅልባት ከተማ መስላለች፡፡  ሲመሽ ደግሞ ቀይ መብራቶች በየሆቴሎች ከተሰቀለው ቀይ የቫላንታይን ቀን መልካማ ምኞት መግለጫና ልዩ ዝግጅት ማስታወቂያ ጋር ተደማምረው ከተማዋን ኤርታሌ አስመስለዋታል፡፡ አዲስ እንግዳ የዓለም የቫላንታይን ቀን ነገ እዚህ ነው እንዴ የሚከበረው? ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ አትፍረዱበት፣ እንደ እኔ ብቸኛ ከሆነ አንዲት ብቸኛ አገናኙት፡፡ አንዳንድ ሆቴሎች (ስም መጥቀስ አልፈልግም፣ ©የቃል ኮፒ ራይት-ኢትቪ) ዘበኞቻቸውን ቀይ ሰንደርያና ኮት ማልበስ ጀምረዋል፡፡ ስጋ ቤቶች ሳይቀር አነጋራቸው ተቀይሯል፡፡ ሚጥሚጣ በማለት ፈንታ-ቀይ ሚጥሚጣ ትፈልጋለህ፣ በበርበሬ ይጠበስ በማለት ፈንታ፣  በቀይ በርበሬ ነው በ አልጫ ይሰራልህ ይሉሃል ( በዚህ አጋጣሚ ዛሬ የባላሁትን ማወቅ ችላችኋል)፡፡ ይህ ሁሉ ዝግጅት እሁድ ቅዳሜ ከተማዋን አተረማምሰዋት ለሄዱት አዲስ አበቤዎችና እዚህ መሽገው ነገን ለሚጠብቁ መሰል ጥንዶች ነው፡፡
ይህን ስመለከት የቫላንታይንን ቀን የማክበር ባህል ለመጀመሪያ ጊዜ በቦሌ ሳይሆን፣  በሆራ ሀይቅ በኩል አድርጎ በመርከብ ወደ ደብረዘይት እንደገባ ብልጭ አለልኝ፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ከሆራ ወደ ፈረንጆች ውስጥ ለውስጥ የሚያገናቸውን መንገድ በማጥናት ላይ ነኝ፡፡
1)   ቫላንታይን ቀን ለምን፡
ፈረንጂን የመከተል አባዜ ካልሆነ በቀር፣ ለፍቅረኛሞች ሁሉም ቀን እኩል ነው፡፡ ቀን ለይቶ የሚወድ ፍቅረኛ ለእኔ ወረተኛ ነው፡፡ አለቀ!
2)  ቫላንታይን ቀን ለምን ቀይ፡
ቀይ በሃገራችን ባህል መሰረት የሀይለኝነት፣ የክፉና፣የጠላትነት መለያ ተደርጎ ይወሳዳል (ቀይ ሽብርን ማንሳት ይቻላል)፡፡ በኢ.ኦ.ተ.ቤ/ን ደግሞ ቀይ የመስዋነት መለያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
እንግዲህ ቀዩ ነገር፤
 በባህላችን መሰረት ለፍቅረኛሞች እስከ ሞት ድረስ እንጋደላለን የሚል ማስጠንቀቂያ ሲሆን፣ በቤተስኪያኑ ትርጉም መሰረት ደግሞ ፍቅረኛሞች ለፍቅራቸው መስዋትነት ለመክፈል ቃል የመግቢያ ምልክት ነው፡፡ ግን በቫላንታይ ቀን ማግስት ተጣልተው የሚለያዩትን ቤት ይቁጠራቸው፡፡  እንደፈለጋችሁ ተርጉሙት፣ያም ሆነ ይህ ግን ቀይ ነገር ለእኛ አገር የፍቅር መግለጫ አይሆንም፡፡ ለእኛ አገር የፍቅር መግለጫ አረንጓዴና ቢጫ ቀለም ነው ( ዘመን መለወጫ፣ መስቀልና እሬቻን ማስታወስ በቂ ነው)፡፡ .
ነገን በጉጉት የምትጠብቁ ውድ ፍቅረኛሞች አንድ ቀኝ ምክር ልምከራችሁ፡፡ ቀይ ነገር ተወዷል አትግዙ፡፡ አረንጓዴ ነገር ግዙ››››…….አረንጓዴ ነገር የመልካም ምኞት ተምሳሌትና ባህላዊ ትውፊት ያለው ቀለም ነው፡፡ ሰሞኑን ቀይ ስጋና ነጭ ስጋ ሳይቀር በዋጋ ጀርባ ለጃርባ ተዟዙረዋል፡፡ በ አንፃሩ ጎመን በስጋ ዋጋው ቀንሷል፡፡
ውድ ቀይ አምላኪዎች፡ ጠብቁ! አዲስ አበባ ስመለስ  “ቀይ ፓርቲ” የተሰኘ ለዲሞክራሲ እስከ ደም ጠብታ ድረስ የማይዋጋ አሪፍ ድርጅት እናቋቁማለን፡፡ ሌሎች አባል ለመሆን ተዘጋጁ፡፡ በጊዜ ሂደት ሳትወዱ በግድ ቀይ ነገርን አምርራችሁ መፍራት ትጀምሩና የ አረንጓዴ ፓርቲ አባል ትሆናላችሁ፡፡ እኔም ከ አንድ ፓርቲ ወደ አንድ ፓርቲ እዛወራለሁ፡፡ በመሃል ግን የሀገሬን ባህል አድናለሁ፡፡ ደግሞ ለጨዋታው……….. (እድሜ…….ሃሃሃሃሃ)…………
.
ለማኛውም የነገውን ታሪካዊ የቫላንታይን ቀን ምሽት ከባድ ዝግጅት እየተደረገ ካለበት “ጎልደን ማርክ ሆቴል” አሳልፋለሁ (….ለማስታወቂያ አልተከፈለኝም)፡፡ ሰው ቀይ ነገር ሲያስብ እኔ ስለ ልምላሜ እያሰብሁ አብሬ አመሻለሁ፡፡ በዓሉን እዚህ ለመታደም የምትመጡ ጥንዶች፣ በቀይ አበባ ምትክ አረንጓዴ የዛፍ ቅርንጫፍ ታቅፎ የተቀመጠ ሰው ካያችሁ እኔ ነኝ፡፡ ይህ የጥሪ ማስታወቂያ ባይሆንም፣ አረንጓዴ አድናቂዎች ከ መጣችሁ አንድ ወንበር ክፍት ነው፡፡ ካልመጣችሁም አንዷን ከ እጮኛዋ ጋር የምትጣላ ሴት እምባዋን በአረንጓዴ ቅጠል አብሼ ወደ ቤቴ እብስ………………….ግን ደግሞ ጠንቀቅ ቀይ ደም እዳይፈስ!


No comments:

Post a Comment