Wednesday, February 15, 2017

በ እንተ ቫላንታይን_ ፪

(እለትና ማግስት)
ከ ግብረ መልስ ወደ ማረፊያ ክፍሌ ስገባ……..የፈጣሪ ያለህ!  ክፍሉ የ ፋሽን ማሰልጠኛ ወርክሾፕ መስሏል፡፡

“የማይጠቅም መሬት ያበቅላል ደደሆ
የፈራሁት ነገር መጣ ድሆ ድሆ”
……..እንዲሉ……..ሁላችንም ፈረንጂ ካመጣው የባህል ወረራ በምንም መንገድ ማምለጥ እንደማንችል ገባኝ፡

ከሃላፊዎች ቀጭን ትዕዛዝ የተቀበሉ የአልጋ ከፍል ሰራተኞች ያለ የሌለ ጥበባቸውን ተጠቅመው የቫላንታይን ቀን እንዴት ከጥበብ ጋር እንደሚገናኝ አልጋው ላይ በሰሩት ዲኮሬሽን ሊያሳዩን ሞክረዋል፡፡…………..አራት ማዕዘን፣ ልብ ቅርፅ፣ዲያጎናል…..ምን አለፋችሁ የሌለ የለም፡፡….ምን አልባት ከ አገልግሎቱ በተጨማሪ ሆቴሉ የዲይዛይን ትምህርት ይሰጣል መሰለኝ፡፡…………ክፍሉ በፅጌረዳ አበባ መዓዛ ታውዷል፡፡ ከ እብድ መሃከል የተቀመጠ ሰው ጤነኛ ነኝ ቢል ማንም አያምነውም፡፡………..የተረዳሁት ነገር ሁላችንም ታመናል፡፡………ጨዋታው የ 6 እና የ 9 ቁጥር ነው፤ ሰዎች በራሳቸው ዕይታ ያያሉ፣ ያዩትንም ያምናሉ፡፡……. ያመኑትን ግን ሌሎችን ካልተቀበላችሁ ብሎ በግድ መጫን ትክክል አይደለም፤ ይህን ለማድረግ መጀመሪያ በሌሎች ቦታ ሁኖ ማየት ግድ ይላል፡፡……ውድ አድማጮች አስተውሉ፣ እኔ በዓሉን አልነቅፍም……..የበዓሉን አንድምታ እንጅ! ተከተሉኝ!

በነገራችን ላይ ቃል በገባሁት  መሰረት አረንጓዴ ቅርንጫፍ ታቅፌ ቀድሜ በ ነገርኋችሁ ሆቴል ምሽቱን ለመታደም ጎራ ብዬ ነበር፡፡ አይገርምም!………………..እንኳን ክፍት ወንበር ጠጠር ቢወረወር የሚያርፍበት ቦታ አልነበረም፡፡ አንዳንድ ጥንዶች የፍቅራቸውን ጥልቀት በ አደባባይ ለማሳየት ይሁን በወንበር እጥረት ተጣምረው የተወለዱ መንታዎች መስለው ከ አንድ ወንበር ተቀምጠዋል፡፡(እዚህ ጋ ጨዋ ልሁን……..ሌላው ነገር ለወሬ አይበቃም፡፡) ለመቀመጥ የሚለቀቅ ወንበር ብናማትርም ወፍ የለም፡፡ ለ 30 ደቂቃ ያህል ሆቴሉ በር ከተገተርን በኋላ፣ ጓደኛዬ …‹‹ባክህ እንሂድ›› አለ፡፡ እኔ ግን እንዲህ ስል አንገራገርሁ…………………‹‹መሄድስ እንሂድ…..ይህን የታቀፍሁትን ለምለም የዛፍ ቅንዛፊ ምን ላድርገው›› አልኩት……..
‹‹ወደ ጓሮ ሂድና ትከለው››…አለኝ ……ፈገግ ብሎ
መጀመሪያ ተናድጄ ነበር……የዘረርሁትን የቃሪያ ጥፊ የፍቅረኛሞችን ቀን ላለመረበሽና በኋላ ለሚፈጠሩት አንዳንድ ጥፊዎች አርያ ላለመሆን ስል ወደ ሰገባው መለስሁት፡፡  ከዚያም …..‹‹ሂድ ዶማ አምጣና ቆፍርልኝ›› አልኩት
‹‹ለ ዘበኞች ስጣቸው ይተክሉታል››…. ብሎኝ መጓዝ ጀመረ፡፡
በኋላ ሳስበው…ጓደኛዬ እውነቱን ነው!….በዛሬ ቀን የተጨፈጨፈውን የፅጌረዳ ዛፍ ለመተካት መንግስት ከ ቫላንታይን ቀን ማግስት የሚተገበር የአረንጓዴ ልማት ዘመቻ ማቀድ እንዳለበት ብልጭ አለልኝ፡፡ ይህን ዘመቻ አንዲት የዛፍ ቅርንጫፍ በዚህ ቀን በመትከል እኔ ልጀምረው ብዬ ወደ ጓሮ ለመሄድ ዞር ስል፤ ከፍቅረኛው ጋር እየተላፋ የሚሄድ አንድ ጎረምሳ ገፈተረኝና የያዝሁት የዛፍ ቅርንጫፍ ወደ መሬት ተነጠፈ፡፡ ………..ይቅርታ አንኳ ሳይለኝ……….አፉን ወደ ልጅቷ አንገት ስር ወሽቆ …..መንገዱን ቀጠለ፡፡  ልጁ ራሱ የሆነ ወሻቃ ነገር ነው!፡፡ …እሱን ቀና ብዬ በግርምት ሳይ …አንዲት እጮኛዋን ፍለጋ ሰማይ ሰማይ የምታይ ኮረዳ ፊዚክስ በማይፈቅደው ጫማ ቅጠሌን ደፍቃው አለፈች፡፡ አሁን የምር ተናደድሁ፡፡
‹የሰማዩን ስንመኝ የመሬቱ እራቀን፣ የመሬቱን ስመኝ የሰማዩ አመለጠን፤ ያልያዝነውን ስናሳድድ የያዝነውን ጣልን፤  የሰውን ስንታቀፍ የራሳችንን ረገጥን…….መንገዳችን ወደየት ነው?፣ መድረሻችንስ የት ነው?………››
…….በሚል ምናባዊ ውዝግብ ውስጥ እራሴን እየጠየቅሁ…..የተረገጠውን የዛፍ ቅርንጫፍ የጎሪጥ አይቼ ተውኩትና ጓደኛዬን ተከተልሁት፡፡
…..ወደ አረፍንበት ሆቴል ስንመጣ እዚህም ተቀውጧል፡፡ ሰገነቱ አካባቢ ቦታ ፈልገን ቁጭ አልን፡፡ ከሰገነቱ ታች ግቢውን የሞላው ሰው በደርዘን ጠጥቶ ከሙዚቃው ጋር በደርዘን ይጮሃል፡፡ ………ጥንዶቹ ሃገርኛውን ዳንስ ወደ ፍስክ እየቀየሩ ይደንሳሉ፡፡ ብዙዎቹ ቀይ ለብሰዋል፣ ቀይ ያለበሱት ደግሞ ሆቴሉ ያዘጋጀው ቀይ ሪቫንና ቀይ ፊኛ ጎን ተቀምጠዋል፡፡ አንዳንዶች ወደ ቀይ ጠጋ ያለ ቀለም ያለው ልብስ ለብሰዋል፡፡ ልበሳቸውን ቀይ ቀለም ነክረው የመጡትንም ታዝበናል፡፡

……………ቀይ ሪቫን ያደረጉ አስተናጋጆች እንደ ተራዳይ መላዕክ ወይም እንደ ነፍስ አድን ሰራተኛ ይራወጣሉ፡፡ ሪቫኑ የሆቴል አስተናጋጅ ሳይሆን የቀይ መስቀል ሰራተኛ አስመስሏቸዋል፡፡ ‹‹‹‹በእርግጥ ይሄም ቀይ መስቀል ነው››››› ……..ከዚህ ሁሉ ትዕይንት ህዝብ በኋላ እጂ ለ እጂ ተያይዘው የገቡት ፍቅረኛሞች (ጓደኛሞች) ሁሉ ተደጋግፈው አንዳንዶች ተዛዝለው መውጣት ጀመሩ፡፡ በእንፃሩ ብቻቸውን ወደ ሜዳው የገቡት የሁለቱም ወገን ፆታዎች ነፃ ተጫዋች በዳንስ ሰበብ እየጨበጡ መውጣት ጀመሩ፡፡ ……………….ይህ ነው እንግዲ ቫላንታይን!........... ከፍቅረኛሞች ቀንነት በተጨማሪ የስራ እድል ፈጣሪ ቀን መሆኑንም ልብ ይበሉ፡፡ ……ዘገባዬን ከመጨረሴ በፊት……ጓደኛዬ ለሚስቱ የፃፈላትን ግጥም በግልብ ላሰማችሁና ሸከፍ ልበል፡፡
‹እስከ ሰባ አመት
በ እርጅና በሽበት
በ ጠብ በድህነት
ፍቅሬ አንለያይም…..እስኪለያየን ሞት››
እውነተኛ አፍቃሪዎች አበባውና ቀዩ ቀሚስ ይቅርና በዚች ግጥም ለፍቅረኞቻችሁ ቃል ግቡ፡፡

ጎበዝ ……………ከወንዙ አፋፍ ላይ ነን ……የገባችሁ ዋኝታችሁ ተመለሱ፣ ያልገባችሁ ወደ ኋላ እንመለስ……………‹‹የሰው ወርቅ አያደምቅ፣ ቢደምቅም አያዘልቅ›› ነው ነገሩ!

No comments:

Post a Comment