Monday, July 24, 2017

ይድረስ ለ 'ጃንሆይ'

እንዴት አሉ ጃንሆይ?
ሰላምታ አቅርበናል~ወደ አሉበት ሰማይ
ዓለም ለሚያከብረው~ ክቡር ልደትዎ
ኬኩ ባይቀምሱም~እንኳ አደረሰዎ
እንኳን የእኛ ሆኑ!

………እንኳን ተወለዱ!
ይህን ጭቁን ህዝብ~እንኳ እንደ ላም ነዱ!

እኔ ምለው ጃንሆይ፡
እንዴት ነው ሰማይ ቤት?
ወዴት ከተሙ ሲኦል ወይስ ገነት?


እኛም ጃንሆይ
40 አመት ተደፍተን~መሬት መሬት ስናይ
አንድ ጩሊሌ አሽከር~እርስዎ ቢሰረቁ
ሹማምንቱ ሁሉ~ እንቅልፋቸው ነቁ

እኛ ህዝቦችዎ፡
ማት ይወርዳል ብለን~ሰማይ ሰማይ ስናይ
ጩሊሌው ቁጭ አለ~ እርስዎ ዙፋኑ ላይ


ከዚያማ ጃንሆይ፣
ዓመት ንገሱየቀመርነው ዜማ
ተራማጅ መዝሙር~በአብዮት ተቀማ
የፈራነው መዓት~መጣ አረፋፍዶ
ስለቱን አሹሎ~ጅራፉን ገምዶ
በሀዘን አስነባት~ይችን ምስኪን ሀገር
ልጆቿን በላባት~ አብዮት መቃብር


ኧረ ተውኝ ጃንሆይ!
አዲስ ነገር የለም~ ኢትዮጵያ ሰማይ!
ያውናት ይች ሀገር~ተሽሎም አልተሻላት
እባክዎት ጃንሆይ፣ ያገኙት እደሆን፣ ጌታን ይለምኑት!


እኔ ምለው ጃንሆይ!
ሰፈሩ ወዴት ነው~ የመንግስቱ ንዋይ?
ያን በላይ ዘለቀን~አይተውት ያውቃሉ?
አሁንም ጀግና ነው~ንዴት ነው አመሉ?

እርስዎን ሲያገኝስ~ሰላም ይልዎታል?
ነው ስራዎን አውቀው~ፈርተው ይሸሹታል?

ማን ነበር ያ ጀግና~ዮፍታሄ ንጉሴ?
ቴአትር ያዘጋጃል~ለእግዜሩ ውዳሴ?
እባክዎ ጃንሆይ፣ ዮፍታሄን ሲያጉኙት
‹‹ተፋጀን›› ሚል ተውኔት፣ ላክልን ይበሉት፤

ያች ብላቴናስ~ዋለልኝ እንዴት ናት?
ከልብ ትሰማለች~አሁንስ ሲመክሯት?
ያች አቤ ጉቤኛስ~የለውጧ መሰላል?
መፅሐፍ አሳተመችተወለድሁኝየሚል፤


ከንኩርማህ ጋራስ ትገናኛላችሁ?
ስለ ጥንቱ ትግል~ምን ምን አዎራችሁ?

እኛማ ጃንሆይ፣
ንኩርማህ ክብር~አንድ ሐውልት አቁመን
ሽቅብ እያየነው~ኤሎሄ እንላለን!
‹‹የኋላው ከሌለ…›› ሚል ትውልድ ሲጣራ

የእርስዎም ‹‹ጃ›› ሐውልት~ታስቧል ሊሰራ
ባይሆን ስንመርቀው~እንዲመጡ አደራ!

ጃንሆይ ይቅር በሉኝ!
የልጅ ነገር ሁኖ~ጥያቄ አበዛሁኝ
ጀግናው ቴዎድሮስ~እንዴት ናት ሽጉጡ?
ሽፍታ ያድናሉ~አሁንም እየወጡ?
እምዬ ምኒሊክ~እንዴት ነው ደግነቱ?
ያች የሸዋ መርፌስ~እንዴት ናት እጣይቱ?
አፄ ዮሐንስስ~እንዴው እንዴት አሉ?
ከንጉስ ሚካኤል~ጋር አሁንም ያወራሉ?


እኛማ ጃንሆይ፡
እጅ ንሱ ስንባል~ለክብራችሁ ስንሰግድ
ወደፊት ስንባል~እ’ልፍ ስንራመድ
የነገሰው ሁሉ~እንደ ነዳን ስንሮጥ
ፀሐይ ነው ስትሉን~ጨለማ ውስጥ ስንዘቅጥ
አንዱ የሰራውን~አንደኛው ሲንደው
አንደኛውን እውነት~አንደኛው ሲሽረው
ያላፊውን መንገድ~ለጊዜ ሲያፈርሰው

አለነ በጅምር!
ከ‹‹ትናንት›› ተጣልተን ‹‹ነገ››ን ስናፈቅር

ኧረ ተውኝ ጃንሆይ!
አቤት የኛስ ስቃይ!
መላ ቅጡ ጠፍቶን~አለን ጎዳና
ኃጢያታችን ጋርዶት~እግዜር መች አየና?
ፍረዱን እናንተ~ይፍረደን ደመና
መንገዱን አሳዩን~ አንድ ምከሩና 
ታርቃችሁ አስታርቁን~በአንድነት እንፅና!
==========================================================

© 2009 ዓ.ም
(መልካም ልደት ጃንሆይ!)


No comments:

Post a Comment