Thursday, January 25, 2018

ቴዲ አፍሮ፣ ወልዲያ፣ ኢትዮጵያ






‹‹ኢትዮጵያ›› በሰቆቃ እንድትኖር የተፈረደባት ምድር ትመስለኛለች፡፡ ቅድመ አያቶቻችን ልጆቻቸውን በፋሽት አረር አጡ፡፡ ‹‹ጥዋ ተርታቸው እድል ፈንታቸው›› ገና የሆኑ አያቶቻችን በህይወት ተርፈው አባቶቻችንን ወልደው አሳድገው ለአብዮት እሳት ገመዱ፡፡ ከአብዮቱ የተረፉ አባቶቻችን በፈንታቸው ልጆችን ወልድው በዘረኝትነት ቋያ አቃጠሉ፡፡ የዘረኝነት ቋያ እያደረ ብዙዎችን ወደ እሳቱ ገመደ፡፡ እስከዛሬ ብዙ ህልም ጨነገፈ፡፡ ብዙ ተስፋ ነጠፈ፡፡ ብዙ የንፁሃን ነፍስ ተቀጠፈ-እዚች ባልቴት ሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ፡፡

እንዴት አንድ ሀገር ተመሳሳይ የሆነ ለቅሶ ከመቶ ዓመት በላይ ታለቅሳለች? እንዴት አንድ ሃገር ለመቶ ዓመት በተመሳሳይ በሽታ ታማ ትሞታለች? ውሎ ሲያደር ሞት ሲለመድ፣ የሰው ልጅ ደም እንደውሻ ደመ ከልብ እየሆነ ቀረ፡፡ እንዴት ሰው የራሱን ወገን ይገላል? ብዬ የሞኝ ጥያቄ አልጠይቅም ግን እንዴት ከመግደሉ በፊት ትንሽ ማሰብ ያቅተዋል?

የቴዲ አፍሮ ኢትዮጵያ የብዙዎች ኢትዮጵያ ናት፡፡ አማራ ያለ ኢትዮጵያ፣ ትግሬ ያለ ኢትዮጵያ፣ ኦሮሞ ያለ ኢትዮጵያ………..ዋጋ የለውም፡፡ ሁሉም ሰው ግን ማንነቱ ተከብሮ በእኩልነትና በመቻቻል ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ካልቻለ፣ ኢትዮጵያ የማንም አትሆንም፡፡ ኢትዮጵያ አንዱ እየበላ ሌላው ጦም ካደረ፣ አንደኛውን ፈረስ አድርጎ ሌላኛው ከሰገረ፣ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ አትሆንም፡፡
በስራ አጋጣሚ ባህርዳር አካባቢ ስለነበርሁ የቴዲን ኮንሰርት የመካፈል እድሉን አግኝቻለሁ፡፡ ቴዲአፍሮ ባህርዳርን በሰላም አሸብሯት ነበር፡፡ መንገዶች ሁሉ የቴዲን ድምፅና ምስል ያስተጋቡ ነበር፡፡ የባህርዳር ብሔራዊ ስታዲዮም የታደመውን ከ 60 ሺ በላይ የሚሆን ህዝብ ስሜት ለማንበብ ሞከርሁ፡፡ ብዙው ሰው የዘፈንና የዳንኪራ ሱስ ይዞት አይደለም ወደ ኮንሰርቱ የገባው፡፡ በድምፃዊው በኩል ብሶቱንና ስሜቱን ለመተንፈስ እንጂ! የብላቴናው ድምፅ የወጣቱ ድምፅ እንደሆነ በስታዲየሙ የከተመ ሰው በቀላሉ የሚረዳው ሃቅ ነው፡፡ በእርግጥ በኮንሰርቱ ውስጥ ሶስት ትውልዶችን ተመልክቻለሁ (አዛውንቶች፣ ጎልማሶችና ቅድመ ወጣቶች)፡፡ ሁሉንም በአንድ ስሜት ያስተሳሰራቸው ሃገራዊ ፍቅር (ኢትዮጵያዊነት) ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሲባል ግን ማንነትን ጨፍልቅ ሉዓላዊነት ብቻ ይታሰባል ማለት አይደለም፡፡ ከአራቱ ማዕዘናት የመጡ የምድሪቱ ልጆች አፍሪካን፣ ሸመንደፈርን፣ ኢትዮጵያን፣ ጎንደርን፣ ሰብልዬን፣ ጥቁር ሰውን… አጥሩ ሳይገድባቸው በአንድ ድምፅ አቀንቅነዋል፡፡ በአንድነት ውስጥ ግን ማንነት መከበር አለበት፡፡ አሊያ እኩል ሚዛን አይኖርም፡፡ 

ወጣቱ ጮክ ብሎ ቴዲ አፍሮን ‹‹ጃ ያሰተሰርያል››ን እንዲዘፍን ጠየቀ፡፡ እሺ እዘፍናለሁ ብሎ ነበር፡፡ የመጨረሻው ውሳኔ ላይ ግን የማናጀሩም እጂ ነበረበት፡፡ አልዘፍንም ብሎ በጥቁር ሰው ጨረሰ፡፡ አንድም ሰው አኩርፎ አልወጣም፡፡ ጥቁር ሰውን አብሮ አዚሞ በሰላም ወደየቤቱ ሄደ፡፡ ውሳኔው ትክክል ነው አይደለም፣ የሚታወቀው ቢዘፍነው ኖሮ ቀጥሎ የሚመጣውን ነገር በማየት ነው፡፡ አሁን ‹‹ቢዘፍን ኖሮ እንዲህ ይሆን ነበር፡፡ ያልዘፈነው ስለፈራ ነው……..እትትት›› ከሚሉ ማላምቶች ውጭ ጉዳዩን መዳኘት ከባድ ነው፡፡  
ከኮንሰርቱ አንድ ቀን ቀድሞ አንድ የባጃጅ ሹፌር እንዲህ ስል ጠየቅሁት
ለሌላ ዘፋኝ እምቢ ብላችሁ ለቴዲ አንዴት ፈቃደኛ ሆናችሁ?
<<ቴዲ እኮ ነው፣ በእሱ ዘፈን ውስጥ የእኛ ድምፅ አለ፡፡ ስሜታችንን ይገልፅልናል፡፡>>
በኮንሰርቱ ከቴዲ ምን ትጠብቃላችሁ?
‹‹ 17ቱን 12 መርፌም ብሎ ይዝፈነው ‹‹ጃ ያሰተሰርያል››ን እንዲዘፍን እንፈልጋለን›› አለኝ፡፡
ወጣቶቹ ‹‹ጃ›› እንዲዘፈን የፈለጉበት የራሳቸው ዓላማ ይኖራቸዋል፡፡ ቴዲ መዝፈኑን የሰረዘበት የራሱ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ ሁለቱም ትክክል ናቸው፡፡ ይህ ማለት ቴዲ ፈርቷል ወይም አላከበራቸውም ማለት አይደለም፡፡ እነሱም ስላልዘፈነ ጠልተውታል ማለት አይደለም፡፡ ቴዲ ሰው እንደመሆኑ መጠን የራሱ ድክመት ይኖርበታል፡፡ ግን ከእነድክመቱ የሚሊዮኖች እስትንፋስ ሆኗል፡፡ ጥሩ የሰሩትን ማሞገስ ካልቻልን ነገ ሰው ማብቀል አንችልም፡፡
ሌላኛው ጉዳይ፣ ‹‹ወልድያ ሰው ሞቶ ለምን ኮንሰርቱን አልሰረዘም፣ ለምን ጨፈራችሁ›› የሚል የብዙሃን ድምፅ በየቦታው ይሰማል፡፡ እውነት ነው፡፡ የብዙ ሰዎች ስሜት ጥሩ አልነበረም፡፡ ትኬቱን ገዝተው ያልገቡም ሰዎች ነበሩ፣ አንድም በፍራቻ አሊያም በሃዘን፡፡ ‹‹ኮንሰርቱን በዚህ ምክንያት መሰረዝ የሽንፈት ምልክት ነው፣ ይህን ሴራ ማለፍ አለብን›› የሚሉም ነበሩ፡፡ ኮንሰርቱ ውስጥ የገባ ሰው ለወልዲያ ሰማዕታት አላዘነም ብሎ ማሰብ ግን ቂልነት ነው፡፡ አስራ አንድ ሰዓት አካባቢ ስታዲየሙ የሃዘን ቤት እንጂ የመዝናኛ ሜዳ አይመስልም ነበር፡፡ ሁሉም ልብ ውስጥ የወልዲያ ያልደረቀ ደም ብቻ ሳይሆን ከ አመት በፊት አባይ ዳር የፈሰሰው ደም፣ በመላው ሃገሪቱ የተቀጠፈው የሰው ህይወት ልባቸው ውስጥ እንዳለ ገፀ ፊታቸውና ድምፃቸው ያሳብቃል፡፡  ሌላው ለየት ያለብኝ ነገር ከኮንሰርቱ ሲወጡ ከሃዘን ቤት የወጡ እንጂ ሲዝናኑ ቆይተው የወጡ አይመስልም፡፡ ለምን? መልሱን የእያንዳንዱ ሰው ልብ ያውቀዋል፡፡
ፈጣሪ የተሰውትን ነፍስ ይማርልን!

ለገዳይም ላስገዳይም ልቦና ይስጠው!

No comments:

Post a Comment