Thursday, January 4, 2018

★አንዱ በር ሲዘጋ....★

ማዕከላዊን መዝጋት ጥሩ ጅምር ነው፡፡ ወደ ሙዚየም ሳይሆን ወደ ሆስፒታል/ትምህርት ቤት መቀየሩ ደግሞ የተሻለ ያስመሰግናል፡፡ ዓለም በቃኝ የአፍሪካ ህብረት /ቤት ሁኗል እንጂ 60 ጄራሎች የተሰውበት ቦታ ተብሎ ሙዚየም አልሆነም፡፡
መጪው ትውልድ የቂምና የበቀል ትዝታዎቹን በረሳ ቁጥር የበለጠ ለአንድነትና ለእድገት ይተባበራል፡፡ ኢትዮጵያም ወደ ቀደመ ክብሯ ትመለሳለች፡፡ ሙዚየም ሳይሆን /ቤት ይሆን፡፡ ትውልድ ይዳን፥ በእኛ ይብቃ ማለት እንልመድ፡፡ (ነገረኛ...ሙዚየሙንስ ማን አየብን የሚል አይጠፋም)፡፡ 

ግድ የለም ተረጋጉ፡፡ <ፈጥኖ ያመነ፥ ቀድሞ ይክዳል> እንዲሉ.....<ፈጥኖ መደሰትም፥ ለሀዘን ቅርብ ነው>፡፡ ይሁን ለጊዜው ይህን መስማት ትልቅ እምርታ ነው፡፡ ነገር ግን ማዕከላዊን ዘግቶ ሌላ ማዕከላዊዎችን ለመክፈት ማሰብ ነገሩን ታጥቦ ጭቃ ያደርገዋል፡፡
እዚህ ላይ የበውቀቱን ሁሌ ከህሊናዬ የማትጠፋ ግጥም ለማስታወስ ወደድሁ፡፡
" ማጭድ ይሆነን ዘንድ ሚኒሽር ቀለጠ
ዳሩ ብረት እንጂ ልብ አልተለወጠ
ለሳር ያልነው ስለት እልፍ አንገት ቆረጠ"
ይላል፡፡
የተቀየረው አነጋገራችን እንጅ አስተሳስባችን አይመስልም፡፡ እርምጃውን ባደንቅም፥ አነጋገር ከግብር ጋር አብሮ ካልሄደ ነገሩ ፍሬከርስኪ ይሆናል፡፡

ቅሊንጦ ፈጣን መንገዱ ጀርባ ለሺዎች ማጎሪያ የሚሆን የእስር ቤት ማስፋፊያ እየሰሩ፥ ዝዋይ ሰማይን ጣራው ያደረገ ጓንታናሞ እየገነቡ፥ ማዕከላዊን ዘጋን ማለት አይንህን ጨፍንና ላሞኝህ አይነት ነገር ነው፡፡
በእርግጥ ወንጀለኛ አይታሰር የሚል እምነት የለኝም፡፡ እስር ቤት ያስፈልጋል፡፡ ግን ለእስር ቤት የሰጠነውን ትኩረት የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ብንታትር ኑሮ የሚታሰርም ባልኖረ ነበር፡፡

የእስር ቤት መብዛት፥ የወንጀለኛ መብዛት በአንድ ሃገር ውስጥ ያለውን የርዕዮተ ዓለም ችግር አመላካች ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አፋጣኝና ዘላቂ መፍትሔ መላ ማለት ጥቅሙ እጥፍ ድርብ ነው፡፡ ጅምሩ የሚመሠገን ነው፡፡ የህዝብን ፍላጎት ማክበር ሀገርን ማክበር ነው፡፡ ሀገር ህዝብ ነው፡፡ ስለዚህ የሚታየውን በር ዘግቶ፥ ስውር በር ከመክፈት ይልቅ ጆሮን ለህዝብ ድምፅ ክፍት ማድረግ ለነገዋ ኢትዮጵያ ሁነኛ መድሃኒት ነው እላለሁ፡፡
በመጨረሻም በአንድ ወቅት ቃሊት ውስጥ ገብቼ ወጣቶቹን ባየሁ ጊዜ ስሜቴን የጫርሁባት ግጥም እንዲህ ትላለች፡፡
"ወጣቱ ቃሊቲ፥ አዛውንቱ ከቤት
ምሁሩ አውሮፖ፥ ልጆች ትምህርት ቤት፤
እህቶች አረብ ሀገር፥ እናቶቹ ማጀት፤
ማን አለ ከመስኩ፥ ከሰብሉ ማሳ
ሀገር ስትቸገር፥ ደግፎ ሚያነሳ?
ብዙው በሱስ ዓለም፥ ሌላው በወሬ ቋት፥
ጠባብ ትምክተኛ፥ በሚል ከንቱ ተረት
አካሉም መንፈሱም፥ ከታሰረ እንደ በግ
ታዲያ በየት በኩል፥ ይች ሀገር ትደግ?"
ምፅፅፅፅ!


No comments:

Post a Comment