Tuesday, July 3, 2018

የሀገሬ መንገድ

                              (Photo: Google)
ወገኛው በኃይሉ ገ/መድህን ‹‹የእኔ እና የሀገሬ ነገር መሬት አልረገጠም›› ብሎ ነበር ከአንድ ሁለት ሶስት ሳምንት በፊት፡፡ አንዳንዱ በቃ ኢትዮጵያ መቼም ወደማይቀለበስ የዲሞክራሲ አስተዳደር ተሸጋገረች ብሎ ይዘምርና ትንሽ ቆይቶ ‹‹እነ እንትና አለቀላችሁ!፣ እነ እንትና እንዲህ መደረግ አለባቸው፡፡ እንዲህ እንዳደረጉንማ በዋዛ አንለቃቸውም፡፡ እንትና ይታሰር፡፡ እንትና ይመርመር! እንትና ይሰቀል››  እያለ ይፎክራል፡፡ ወገን ዲሞክራሲ እና ፉከራ አብሮ አይሄድም፡፡ ዲሞክራሲ ‹‹ከፍፁም ይቅርታ እና መቻቻል የሚፈጠር የማህበረሰብ ደልድይ ነው››፡፡  የሆነ ቦታ ላይ ሁሉንም ነገር በይቅርታ ማራገፍ ካልተቻለ፣ ቂምና በቀል ጅረት ነው-ማቆሚያ የለውም፡፡ ጅረቱ ውቅያኖስ ውስጥ ተጠራቅሞ አንድ ቀን ነፋስ ሲንጠው፣ ማዕበሉ የሚያመጣው ቀውስ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በትንሹም ቢሆን ቀምሰነዋል፡፡ 
የደቡብ እና የመሃል ሀገሩ ህዝብ በአንድነት ‹‹እድሜ ለአብይ፣ የዲሞክራሲ ቀን መጣ›› እያለ የመኸሩን ደመና በሰንደቅአላማ ሲሸፍን፣ ከወደ ሰሜን ደግሞ ‹‹የጦርነት አዋጅ ጥሪ›› በሚመስል መልኩ ነጋሪት የሚጎስሙ ሰዎች በቀጥታ ስርጭት እያየን ነው፡፡ በመበሻሸቅ ወደ ፊት የቀጠለ ሀገር የለም፡፡ በመበሻሸቅ ውስጥ ‹‹ ባልበላውም ጭሬ አፈሰዋለሁ›› የሚል ስነልቦና ይፈጠራል፡፡ ግን ሁሉም ነገር የሆነ ቦታ፣ የሆነ ቀን ሀገራዊ በሆነ መግባባት ተዘግቶ ወደፊት መራመድ ካልተቻለ፣ ሁሉ ነገር ‹‹የህልም ጉዞ›› እንዳይሆን እፈራለሁ፡፡

መቼም ይሄ ህዝብ ‹‹ ማንበርም፣ መቅበርም›› የተካነበት ነው፡፡ ግን ሁሉም ነገር ከስሜት በፀዳ በአመክንዮ ቢሆን መልካም ነው፡፡  ስለዚህ ከስሜት ተመልሶ፣ የነገውን መንገድ በእስተውሎት እና በጥንቃቄ መቀየስ፣ ክረምቱ ሳይገባ ድልድይ መስራት፣ ወደ ነገ ለመሻገር ወሳኝ ምዕራፍ ይመስለኛል፡፡አሊያ ጉዟችን ሁሉ ፔንዱለም እንዳይሆን እፈራለሁ

No comments:

Post a Comment