Sunday, April 26, 2015

የመንገደኛ ነፍሶች ዋይታ

             ከ ጦቢያው አለም
ከወሎ ከሀረር፣ ከወለጋ ከወላይታ….ወጥተን
የደንበልን ሸለቆ የሱዳንን ጥሻዎች አቆራርጠን
በቀይ ባህር አዞዎች በየመን ግርዶሾች ተውጠን
ሞተን ተርፈን ሳውዲ አረቢያ ገብተን
ጉልበታችንን ሽጠን በልተን
በእንባችን ልብስ እያጠብን
ወዛችን ሽቶ ሆኖን ለራሳችን የነጻን ሲመስለን ለሌሎች ከርፍተን
በረሀ የበላው ጸጉራችንን ነጭተን ማግደን ሳት አንድደን ሞቀን
ነደን አብስለን በልተን አብልተን ሁሌ ሞት ሲፈረድብን

መልሽልን እንጂ እማ ሰሚን-ጥሪን-እንሰብሰብ
አየሽ እማ የግዮን ወንዝ ተፍቶን
ከቀይ ባህር አዞዎች የትንቅንቅ ግሳት ተርፈን
ካʼፓርታይድ መንደር ተጥለን
ሱቃችን ተሰብሮ ተወሰደብን
አፍሪካ እያልን ነጻነትን ስንዘፍን
እማ ነይና እይው አንዴት አንደሆነ ሞት
ስጋችንን ጎትተው አንድደው ሲሞቁት
ደግሞ በአዋሽ ልብ ተረገዘን በምጥ ጣር ድንበር አልፈን ተወልደን
በራብ ተንጋደን ስንሄድ በበረሀው አፋፍ
በሊቢያ የምንፈጥረው ጎርፍ
እንዲህ እየተቀላን በሰይፍ
እይን እስኪ በደም ታጥበን ሟሙተን ስንኳርፍ
አኮ እማ እስከመች ነው የሚጮከው
እኮ እስከመች ነው እንባችን የሚፈሰው
እማ እስከመች ነው ተስፋችን እውን የማይሆነው
㙀㙀㙀㙀㙀㙀㙀㙀㙀㙀㙀㙀㙀
ጠባቂ መልእክቶችሽ እየሸጡን ለብር
አንጉዋለው ለይተውን ከዘር
ወጥተን ተሰደን ከሀገር
ላʼውድማቸው ሆነን የገለባ አጥር
ምስጥ በልቶን በመንገድ ስንቀበር
እኮ እማ እስከመች ይብላን ባእድ አፈር
በሀገርስ ስንኖር
ህንጻ ስንሰራ ያሳርፈናል ብለን ጥላሽ
ወድቀን ስናፈርስ ያʼሮጌውን ቤትሽ
ስንሰራው ሚጥለን ድንጋዩን እያየሽ
ስነተራመስ በመኪና አደጋው በሰልፉ ግርግር
ድከን ስናቋርጥ በመነገዶችሽ ዳር
ሽፋሽፍቶቻችን ሳይከደኑ ተገፍተን
አለቅን ገብተን በገደሎችሽ ሸገር
ደግሞ ብንተርፍ ከገደልሽ
የምሽቱ ግርዶሽ ሲከበን
የማይነጋው ሌሊት ግርማው እያስፈራን
እኮ እስከመች አንደዚህ ታፍነን
ገርበብ ሲል እያዩ የአራት ኪሎ የካህን ሰፈር ጅቦች
ጮኸው እየበተኑን(ሲያስበረግጉን) በጠባቡ ስንፋጅ
የገደሉ ጎጇችን ደግሞ ደጋግሞ ሲፈርስብን ያላዋጅ(ባዋጅ)
ወዲያ ተወዲ በደም አንድ ሆነን ተሳስረን
ተለያይተን በቁዋንቋችን ቁጥር
ሂሳብ ለማወራረድ ስንኖር
ተገራርደን በአመለካክታችን አጥር
ሞተን ተቀብረን
ደግሞ ነቅተን የበቀል ሀውልት አቁመን
አኮ እስከመች እንዲህ አንዘልቃለን
እይ እማ ስንፍናችን አስተኝቶን በስብሰን ፈርሰን
በእንባችን አጠጥተን መታረጃችንን አብቀለን
እኮ እስከመች ረሀቡ
እኮ እስከመች ስደቱ
እኮ እስከመች መለያዬቱ ይቅጠፈን
አኮ እማ እስከመች ነው የሚጮከው
እኮ እስከመች ነው እንባችን የሚፈሰው
እማ እስከመች ነው ተስፋችን እውን የማይሆነው
㙀㙀㙀㙀㙀㙀㙀㙀㙀㙀㙀㙀㙀
አለቆችሽ ሸጡን
መንገዱ አስቀረን
በረሀው አቃጠለን
ውሃው በላን
ባህሩ ዋጠን
ገደሎችሽ ጎረሱን……
ኧረ ስንቱ የተሳፈረውን የሞት ታክሲ
ስንቱንስ ሂያጅ ቆጥረሽ ልትጨርሺ………
ሀዘን ይብቃን እማ…እሮሮ ጆሯችን አይስማ
የመነመነው ተስፋችን አይቆረጥ እንጂ እማ
እንምጣ አለሁ በይን ሰብስቢንʼማ
ህፃናቱ የታሉ ማይጫወቱ
እማ ጎልማሶችሽ አሳሱን
ጥሪያቸው ወጣቶሽ ናፈቁን
አረጋውያንስ በየተ ተጠለሉ
ንገሪን እማ
ስንቶች ቆሰሉ ስንቶችስ ሞቱ
እማ ጀግኖቹ ስንት ነበሩ
ቁጠሪያቸው ምሁራኖችሽ የት ገቡ
ጥሪያቸው እንጂ እማ በስማቸው
አሳይን አፈር የበላውን ደማቸውን እንፈሰው
የተከሰከሰ አጥንታቸውን ለቅመን እንቅበረው
የት ናቸው እማ?
አኮ እማ እስከመች ነው የምንጮከው
እኮ እስከመች ነው እንባችን የሚፈሰው
እማ እስከመች ነው ተስፋችን እውን የማይሆነው
ሁላችን እስክንሰደድ?
ሁላችን እስክንሞት?
ወይስ እስከ ምጻት?
ስደት በቃችሁ ሞት አይያችሁ በይን ከልብ
ቃለ ግቢልን ከዚህ በኋላ አንድ ነፍስ አይጠፋ
ይህም ሂያጅ ያልፋል ሌላው ሲመጣ እንዳንከፋ
ሀዘን ይብቃን እማ…ደሙን አይናችን አይየው እሮሮውን ጆሯችን አይስማ
                                ሚያዚያ 2007 .




No comments:

Post a Comment