Thursday, August 20, 2015

“5 ብር በዕለተ ደብረታቦር"

(ለግብርና መር ፖሊሲያችን)
አምስት ብር እንደኔ የሌላችሁ አምስት ጊዜ በከንፈራችሁ ታጨበጭባላችሁ፡፡ ለማንኛውም ተከተሉኝ፡፡ ማጣት አይኑ ይጥፋ (አይን ካለው ማለቴ ነው) ድህነት ገድል ይግባ፤ ኧረ እንጦሮጦስ ይግባ::
               “ካላጡ ካልተቸገሩ
               መኖር ማን ይጠላል በአገሩ…”
ማንአልቦሽ ዲቦ በተስረቀረቀ ድምፅ ከዘፈነቻቸውና በልጅነቴ ከሰማኋቸው ዘፍኖች አንዱ ነው፡፡ ዛሬ ብትኖር ብዙ ትመርቅልን ነበር፡፡ አፈሩን ገለባ ያድርግላት፡፡ አሜን በሉ፡፡ አውነት ነው፤ ድህነት ባይኖር፣ ረሃብ በር ባያንኳኳ ማን ቀዬውን ጥሎ ይሰደዳል፡፡ ያውም አርሶ ጎተራ ሙሉ፤ ነግዶ ኬሻ ሙሉ ያፈሰበትን ቀዬ፡፡ ያውም ሳይሰስት አገርና ወገን የቀለበበትን ቀዬ፡፡ ያውምባድማውን ያብላህ!” ተብሎ የተመረቀበትን ቀዬ፡፡ ዕለተ ረቡዕ ባዕለ ደብረታቦር፣ ነሐሴ 13 2007 . ከምሽቱ 1215 ብሔራዊ፡፡ ደግነት ፊታቸው ላይ የሚነበብባቸውና የደስደስ ያላቸው ሁለት ምስኪን ገበሬዎች ወደኔ ተጠጉ፡፡ ወንድም-ዓለም! የሚል ድምፅ ከአቀርቀርሁበት የሞባይል ሜዳ አባነነኝ፡፡
ይህን ድምፅ በአንድም ይሁን በሌላ አውቀዋለሁ፡፡ የአዲስ አበቤ ድምፅ አይደለም፡፡ ቀና ብዬ ተመለከትኋቸው፡፡ በመለማመጥ እይታ አይናቸውን ላይናታች እያቃበዙ እጃቸውን ዘረጉ፡፡ ወንድም እባክህ እርቦን ነው የዳቦ? እይታቸውና ሰለለ ድምፃቸው በአንድ ላይ ሲደመር አጥንትን ዘልቆ ይገባል፡፡ ማንም ቢሆን ኖሮት የዘረጉትን እጃቸውን አፍረት ባይከለክልምይግዜር ይስጣችሁንወይምከንፈር መጠጣውንየሚነፍጋቸው አይኖርም፡፡ እኔ ግን ኪሴን እየዳበስሁ፣ በጥያቄ አጣደፍኋቸው፡፡
ለምን ጉዳይ መጣችሁ ነው?
ለስራ፡፡
ታዲያ ለምን አሰሩም?
ይኸው ብንነሳ ብንወድቅ ስራ አጣን፡፡ በዚያ ላይ ለአገሩ ለወንዙ ባዳ ነን፡፡
ከየት መጣችሁ ነው?
ጎንደር
ከዚህ በላይ ማናዘዝ አልፈለግሁም፡፡ ባይቸግራቸው ኖሮ እንደ እሳት የሚፋጀውን የሰውን ልጅ ፊት አያዩም ነበር፡፡ እነሆ ትናንት በዳውላ ሰፍረው፣ በሳህን ቸርችረው አገር ያጠገቡ ምስኪን ገበሬዎች በመዳፍ እየለመኑ ፊቴ ላይ ቆመዋል፡፡ በሞሰብ አቅርበው በሞቴ ብላልኝ ብለው የለመኑ ደግ ገበሬዎች፣ ዛሬ ለዳቦ ልመና ቆመው ማዬት ያማል፡፡ በእርግጥ ይህ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ግብርናውን ትተው፣ ጥማድ ፈተው፤ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደ መሃል ከተማ የሚመጡ ገበሬዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ ከዛሬው ትዝብቴ በግምት ከሁለት ወር በፊት ወደ አንድ ቤተክርስቲያን ለመሳለም ጠጋ ስል 10 በላይ የሆኑ አርሰው የሚደክሙ የማይመስሉ ገበሬዎች በተራ ተሰልፈው ሲለምኑ ተመለከትኩ፡፡ ለጊዜው ውስጤ በጥያቄ ይናጥ ነበር፡፡ ስራ ጠልተው መጠው እየለመኑ ነው? ለምን አዲስ አበባ የቀን ስራ አይሰሩም? ለምን ወደ ቀያቸው አይመለሱም? ይህ የኔ መላምት ነው መልሱ ግን በእነሱ እጂ ነው፡፡

አሁን ግን እንዳች ጥያቄ በውስጤ እየተመላለሰ ነው፡፡ የት ነን? ግብርና መር ኢኮኖሚያችን የት ነው? በትክክል የግብርናው ኢኮኖሚ አሁን ላለንበት የኢንዱስትሪ አብዮት ግባት ሁኗል ወይ? ካልሆነስ የአገሪቱን 80% የህዝብ መጠን የሚሸፍነውን ገበሬውን ያማከለ የኢኮኖሚ ስርዓት እንዴት መዘርጋት አለበት? ይህ የእኔ ጥያቄ ብቻ አይደለም፡፡ ለሀገር እድገት እናስባለን ለምንልና ነገ የተሻለች ኢትዮጵያን ማዬት ለምንፈልግ ሁሉ መመለስ ያለበት/ያለብን ጥያቄ ነው፡፡ እጅን ቆርጦ ሙሉ አካል አለኝ ማለት ሞኝነት ነው፡፡ ይህ ትችት ብቻ አይደለም፣ መፍትሔውንም ለማፈላለግ እንጂ፡፡ ሁሌ ስለጨለማ ማውራት መፍትሄ አያመጣም፤ ሻማም ቢሆን መለኮስ ግን ጊዜያዊ መፍትሔ ነው፡፡ እኔ ሁለት ስህተት የተሰራ ይመስለኛል፡፡
1) ጋሪው ከፈረሱ የቀደመ ይመስለኛል፡፡ የግብርና ምርታማነትን በምንፈልገው መጠን ሳናሳድግ ኢንዱስትሪው ቀድሞ ቦታውን የያዘ ይመስለኛል፡፡ ይህም በመሆኑ ግብርና መር ኢንዱስትሪ (agricultural lead industrialization) የምንለው ፖሊሲ ሳይሳካ የቀረ ይመስለኛል፡፡ ለዚህም አንድ ማሳያ የሚሆነን አሁን አገራችን ውስጥ ያሉ ብዙ ፋብሪካዎች ለግባትነት የሚጠቀሙባቸውን  ዕቃዎች በብዛት የሚያስመጡት ከውጭ አገር መሆኑ ነው፡፡ በግብርና ላይ የተመሰረተ የኢንዱስትሪ አብዮት በትክክል ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ አብዛኛውን የኢትዮጵያን ገበሬ ከድህነት ለማውጣት ቁልፍ ሚና ይጫወት ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ እንኳን ለኢንዱስትሪ ግባት ለዕለት ጉርስ የሚሆን ቁራሽ አጠው የከተሜውን በራፍ ደጅ የሚጠኑ ምስኪን ገበሬዎች ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ግን ለኢንዱስትሪ ግባት የሚሆኑ ምንም አይነት የግብርና ውጤቶች የሉንም ማለት አይደለም፤ ቢኖሩም ግን አብዛኛውን አርሶ አደር ማዕከለ ያደረጉ አይደሉም፡፡
2) የኢንዱስትሪ አብዮታችን ገበሬውን ያላማከለ መሆኑ ነው፡፡ አብዛኞች ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጉት የሰው ጉልበት አናሳ ነው፡፡ አለው የዓለም ስልጣኔ አኳያ የምንጠቀምባቸው ላቅ ያሉ ዘመናዊ መሳሪያዎች (Advanced machineries) የሚያስፈልገውን የሰው ጉልበት ቀንሰውታል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢንዱስትሪዎች ከተወሰኑ በትምህርት ከሰለጠኑ ባለሙያዎች ውጭ ያለንን ርካሽ የሰው ጉልበት እንደ ልብ መጠቀም አልቻሉም፡፡
መፍሄው
1) ገልብጠን ብናስብስ፡፡ አሁን ደግሞ ኢንዱስትሪው ግብርናውን ቢመራው (Industry lead Agriculture)፡፡ ምርታማነትን ለማሻሻል የሚጠቅሙ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን በአግባቡ ጠቃሚነታቸውን በመፈተሽ፣ እደግመዋለሁ ጠቃሚነታቸውን በመፈተሽ ተግባራዊ ብናደርግ፡፡

2) እርካሽ የሰው ጉልበት መጠቀም የሚችሉ (Labour intensive) ኢንዱስትሪዎችን ማቋቋም፤ ሁሉን አቀፍ የሆነ እድገት ከማምጣት አኳያ አስተፅኦ ይኖራቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡

በአንድ ነገር እንስማማ፡፡ ምንም እንኳ፣ እኛ ተማርን አወቅን የምንል አውቆ አጥፊዎች የፈጠርናቸው የእርስ በርስ አጥሮች ቢኖሩም ከመቀሌ አስከ ሞያሌ፣ ከሶማሊያ አስከ አሶሳ፣ ከሁመራ እስከ ደሎና ቦረና በየትኛውም እቅጣጫ ብትሄዱ የኢትዮጵያ ገበሬ ከመልካም ደግነቱ፣ ሰብዓዊነቱ ፅኑ እምነቱ ጋር የኖረ ደግ ህዝብ ነው፡፡ ይህን እውነታ ኢትዮጵያን ዞሮ ያዬ በአምስት ጣቱ ይፈርምልኛል፡፡ ይህ ደግነቱ ግን ትናንት ጭሰኛ ተብሎ ከመሰቃየት፣ ዛሬ ደግሞ የኢንዱስትሪው ባይተዋር ከመሆንና የከተሜውን ህይወት አሻቅቦ እያዬ ከመኖር አልታደገውም፡፡ ለዚህም ነው እነዚህ ሁለት ደግ ገበሬዎች በእለተ ደብረታቦር ሙልሙል ዳቦ የቸሩበትን እጃቸውን ቁራሽ ዳቦ ልመና ወደ ፊቴ የዘረሩት፡፡ እኔም ከኪሴ የነበረችዋን አምስት ብር "በግብርና መር ፖሊሲያችን ” ስም መፅውቼ ወደ ቤቴ ገባሁ፡፡ እናንተም ብር ያላችሁ ከኪሳችሁ፣ የሌላችሁ በከንፈራችሁ መፅውቱ፤መስጠት ቤት አይፈታምይባል የለ…ድሮ ድሮ፡፡ ግን ምፅዋት ዘላቂ ለውጥ ያመጣል???
                        ክብርና ሞገስ ለኢትዮጵያ ገበሬዎች!        
                                  ነሐሴ 13 2007 .



No comments:

Post a Comment