Monday, August 17, 2015

የ “7” አንድምታ

በአዕማደ ምስጢር በመፅሐፍ ትርጓሜ
በአቋቋም ሰዓታት በቅኔ ዝማሜ
የሰባትን ቁጥር ሚስጢሩን የሚያውቁ
ይተረጉሙታል ሊቅ እያጠየቁ፤
””””””””””””””””””””””
ለአገሬ ግን ቅኔው ክፉኛ ከበዳት
ይሄ ሰባት ቁጥር ደግሞ ደግሞ ጣላት
ወርቁን ከሰሙ ጋር መለየት አቃታት፤
”””””””””””””””””””””””””
እንግዲህ ወገኔ ልብ ብለህ ተመልከት
በፊት ሀያ ሰባት ኋላም አምሳ ሰባት
ከዚያም ስልሳ ሰባት እስከ ሰባ ሰባት
ከዚያም በሰማኒያ በዘጠና ሰባት
ዛሬም በድጋሜ ሁለት ሰባት
ሰባት ጊዜ መጥቶ ሰባቴ የጣላት
ስውራዊው ሚስጢር የቅኔ ድግማት
ለሊቅ የከበደ ቅኔው ያልተፈታ
ምንድነው ትርጓሜው የሰባት አንድምታ?፤
””””””””””””””””””””””””””””
አልቻልንም ከብዶናል ሆኗል ሚስጢራዊ
እባክህ አግዘን ዮሐንስ ገብላዊ
ንገረን ተዋናይ የቅኔ አበ በኩር
ቅኔን እንደዋዛ ያን ጊዜ ስትፈጥር
የሰባት አንድምታ ትርጓሜው ምን ነበር?
””””””””””””””””””””””””””””
እንግዲህ ወገኔ፤
በሊቅም በደቂቅ በቅኔ መርጌታ
እንዲህ ለዘመናት ቁጥሩ ካልተፈታ
ተሰሃለነ እንበል ወደ ሚስጢር ጌታ
ከእሱ እንዲመጣልን የሰባት አንድምታ
                           
                                        ነሐሴ 09 2007 .
                    መታሰቢያነቱ፡ 
                               በተለያየ ጊዜ በድርቅ ሰለባ ለሆኑ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ይሁንልኝ፡፡

              

No comments:

Post a Comment