Monday, September 7, 2015

"ና መስከረም ግባ"

ና መስከረም ግባ
  ና ሆድህ አይባባ    
ግባ ችግር የለም  
በአንተ አንጨክንም፤
መስከረም ለምለሙ የወራቶች በኩር
የሰላም የፍቅር የህዳሴ ሚስጢር
የዘመን ተምሳሌት የአንድነት ምልክት
የውጥን መባቻ የሐበሻ ኩራት
ኮተትህን ጥለህ መስከረም ሆይ ግባ
ጳጉሜ ላይ ቀብረኸው የጥላቻን ካባ፤
  ና መስከረም ግባ
  ና ሆድህ አይባባ
  ግባ ችግር የለም
  በአንተ አንጨክንም፤
ክፍፍል ጥላቻ መለያያት ይቅር
መከራ ድህነት ይውጣ ከዚች ምድር
ትውልዱ ይቦርቅ በሰላም በፍቅር
መስከረም ሆይ ግባ ወደኋላ አትቅር
በተስፋ መግበው የሐበሻን ምንዝር፤
  ና መስከረም ግባ
  ና ሆድህ አይባባ
  ግባ ችግር የለም
  በአንተ አንጨክንም
ግባ በለምለሙ በአበቦች ፀዓዳ
አንተማ አዲስ ነህ በየአመቱ እንግዳ
እኛ አለን እንጂ የዘመናት ባዳ
ዘመን እየቆጠርን ዘመን የምንከዳ
  ና መስከረም ግባ
  ና ሆድህ አይባባ
  ግባ ችግር የለም
  በአንተ አንጨክንም
አስኪ ልጠይቅህ አድምጠኝ ግድየለም
ከአምና ከታች አምና ከቀዳሚው ዓለም
የተለየ አምሃ ለሃገር ሚጠቅም
ምን አመጣህልን ዘንድሮ መስከረም?
  ና መስከረም ግባ
  ና ሆድህ አይባባ
  ግባ ችግር የለም
  በአንተ አንጨክንም
አደንግጥ መስከረም-ተወው ግድየለህም
መግባትህ አይቀርም-እኔ ባልጠይቅህም፤
ባይሆን መስከረም ሆይ-ወደእኛ ስትመጣ
ኮርማ ፍየል ዳቦ-እኛን ከምትቀጣ
አንተም የድርሻህን-ውለታ ዋልልን
አስተዋይ ልብና- ህሊና መፅውተን (2)!
*********************************
    ጳጉሜ 1፣ 2007 ዓ.ም

(ለማህበራዊ ድህረ ገፅ ጓደኞቸ በሙሉ ለ2008 ዓ.ም  የአዲስ ዓመት መታሰቢያ)

No comments:

Post a Comment