Tuesday, April 19, 2016

ነጭ አምላኪነትና የወገን ፍቅር (White worship & Fellowship’ Love)

“ሳንርቅ እንጠይቅ…..” 
(ከ ዘላለም ጥላሁን)
 ##በቅድሚያ መንግስት ያወጣውን ብሔራዊ የሐዘን ቀን መሰረት አድርጌ የንፁሃንን ነፍስ አምላክ እንዲምር ዝቅ ብዬ የህሊና ፀሎት አድርሻለሁ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ግን አንዳንድ ትዝብቶቼን ልተንፍስ፡፡
ከ ጥቁርና ከነጭ ሰው ማን ይበልጣል???
ይህን ጥያቄ ለመመለስ የሰው መጀመሪያ የነበሩት አዳምና ሔዋን መልካቸው ምን አይነት እንደነበር ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ለ አቤልና ቃዬል የጠብ መነሻ ተደርጋ የምትወሰደው እንስት እንኳ ስለ ውበቷ መልከ መልካምነት እንጂ ስለ ነጭና ጥቁርነቷ የሚገልፅ ማስረጃ የለም፡፡

ያም ሆነ ይህ ግን መች እደተጀመረ ባይታወቅም የነጭ የበላይነት በዓለም ላይ ለ ዘመናት ገኖ/ሰልጥኖ ቆይቷል፡፡ ምንም እንኳ የሰውን እኩልነት የሚያንፀባርቁ ለቁጥር የሚያታክቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ና ድንጋጌዎች በየጊዜው ቢወጡም የሰው ልጅ ግን አሁንም ድረስ ከ አካላዊ ባርነት ቢወጣም ከ አስተሳሰብ ባርነት ሊወጣ አልቻለም፡፡ ይህ ጉዳይ ደግሞ ወደ አፍሪካ ሲመጣ መረን የለቀቀ ችግር ሁኖ ይስተዋላል፡፡ ያን የሰቀቀን የቅኝ ግዛት ዘመን በግፍና በመከራ ያለፉ የአፍሪካ ሀገራት ዜጎች አሁንም ቢሆን ነጭን ከማምለክና ለነጭ ከማጎብደድ (ሮበርት ሙጋቤን አይጨምርም…..) እንዲሁም ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ከማዬት አስተሳሰብ አልወጡም፡፡
ከዚህ አንፃር ሲታይ ኢትዮጵያውያን በተከፈለላቸው የደም መስዋትነት ከዚህ አጥር የመውጣት የተሻለ እድል ነበራቸው-ከዚህ አዘቅት ወጠዋል ብሎ ለመናር የሚያስደፍር ባይሆንም፡፡ ይህንን እውነታ በአንድ ወቅት ከ አፍሪካ ሃገራት ከተሰበሰቡ ወንድሞቼ ጋር ስናወራ አንድ ከ ማላዊ የመጣ ወንድም የተናገረው የቁጭት አስተያየት ሁሌም ድቅን ይልብኛል፡፡ እንዲህ ነበር ያለው፡
“ ኢትዮጵያውያን የተሻለ ተስፋ አላቸው፡፡ ከጥንት አባቶቻቸው የመጣው ባህል፣ ማንነትና ታሪክ ሳይበረዝ ቆይቷቸዋል፡፡ የእኛ ባህል፣ ማንነትና ታሪክ በነጮች ተበርዟል፡፡ ባህላችን ብቻ ሳይሆን አስተሳስባችንንም በርዘውታል፡፡ ሁሌም ከነጮች በታች እንደሆንን አድርገን እንድናስብ አድርገውናል፡፡ ይህንንም አብዛኞቻችን አምነን ተቀብለናል፡፡ አቅም እያለን እንኳ ከ እነሱ ማነሳችንን እኛው ራሳችን እንመሰክራለን፡፡ በ አካል ቅኝ ከተገዙት አባቶቻችን በላይ የእኛ ዘመን ትውልድ የአስተሳሰብ ቅኝ ግዛት የከፋ ይመስለኛል፡፡ አባቶቻችን የጠሉትን ቅኝ ግዛት እኛ ሳናመነታ ዘው ብለን ገብተን እየተቀበልነው ነው፡፡ በዚህ ግን ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ አላት፡፡ ወደ ቀድሞ ማንነታችን ለመመለስም ኢትዮጵያ ለእኛ ትልቅ አርዕያ የምትሆን አገር ናት፡፡ ምንም እንኳ የጥንት ማንነቷ በተለያዩ ምክንያቶች ጥላሸት ቢለብሱም……..”

ወደ ሰሞኑ ጉዳይ ልመለስ፡
ሰመኑን ከጎኔ ታክሲ ውስጥ አብራኝ ትጓዝ ለነበረች ልጅ ጋምቤላ 140 ሰው ተገደለ የሚለውን ዜና አጋራኋት፡፡ ……እሷም አስከትላ…………… “ተቀጠረ ነው ያልክ” አለችኝ…….(በጉጉት ነገሩን ለማጣራት ወደ እኔ በትኩረት እየተመለከተች)፡፡ አይ አይደለም ሞተ ነው ያልኩሽ አልኳት…….
“ነው…..” አለችኝና ፊቷ ቀልበስ አደረገች፡፡ (ከፊቷ ይታይ የነበረው ተስፋ በአንድ ጊዜ ተኖ ሲጠፋ ታየኝ)፡፡ ምነው ምንም አልገረመሽም አልኳት?
“የሞቱት ይሻላሉ፡፡”
እንዴ ምን ለማለት ፈልገሽ ነው? አልኳት ኮስተር ብዬ::
“እኔ አለሁ አይደል በቁም የሞትሁት፡፡ ንገረኝ እስኪ ዳቦ የማያበላ ዲግሪ ታቅፌ በራብ የምሰቃይ፣ የሰው ፊት የሚገርፈኝ፣ የቤተሰቦቼን ተስፋ የበላሁ…………ንገረኝ የት ልሂድ?……….”
ኧረ ተይ ይህንና አለመቀጠርን ምን አገናኛቸው፤ አንቺ እኮ ነገ ትቀጠሪያለሽ ብዬ ንግግሯን አቋረጥኋት፡፡ “……አየህ ያላዬና ያልደረሰበት ሰው አይገባውም፡፡ አንድ ቀን ጦምህን ብትውል ያኔ ትረዳኛለህ..”……..ብላኝ እንባ ያቀረሩ አይኖቿን ወደ በሩ አስቀድማ ፌርማታዋ ላይ ስለደረሰች በንዴት ተሸቀንጥራ ወረደች፡፡
ንግግራችን አልተቋጨም፣ ብዙ ጥያቄዎችን ልጠይቃት ነበር፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው፡፡ … “የራበውን ሰው  ምንም ሳያደርጉ ጥያቄ መጠየቅ ከራቡ በላይ የሆነ በደል መበደል….” ስለሆነ የበደለኝነት ስሜት ተሰማኝ፡፡ አልፈረድሁባትም፣ አዘንሁላት አንጂ፡፡ የዚች ልጅ ንግግር ግን ምን ያክል በጉያችን የተወሸቁ የቀን ተቀን ችግሮች ከ ሰብዓዊ አስተሳስብ እንዳወጡን አንድ ማሳያ ሊሆን ይቻላል፡፡

ግን ምንም እንኳ ችግራችን እንደ አሎሎ ቢከብድም የማላዊው ወንድሜ እንዳለው ያልተበረዘ ባህል፣ ማንነትና ታሪክ ለማህበራዊ ሰላም ያለው አስተዋፅኦ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ እየራበንም ቢሆን የሰውን አንነካም፡፡ ኢትዮጵያውያን ለሃይማኖታቸውና ለባህላቸው ተገዢ ናቸው (ሁሉን ባያካትትም)፡፡ ይህ ባይሆን ኑሮ፣ ፒያሳ ወርቅ ቤት ተደግፎ የሚያዛጋ የጎዳና ተዳዳሪ፣ ባንክ ቤት ተደግፎ በራብ የሚያቃስት የኔ ቢጤ፣ “ሀ” ን በማይፅፍ ዱዳ ባለሃብት እየተሰደበ የሚሰራ ምስኪን ባለ ዲግሪ አይኖርም ነበር፡፡ የትናንት አሻራ ለዛሬ ያለው ዋጋ እንዲህ በቀላሉ የሚሰፈር፣ በቃላት የሚዘከር አይደለም፡፡
ከዚህ ጎን ለ ጎን ግን ድህነት፣ የኑሮ ግሽበት፣ የእርስ በርስ ሽኩቻና የመሳሰሉት ነገሮች በ ጥንት አባቶቻችን የናቁት የቅኝ ግዛት ማጥ ውስጥ ዘው ብለን አንድንገባ እያደረጉን ነው፡፡ አባቶቻችን ወግድ ያሉትን የነጭ የበላይነት እኛ በእጄ ብለን ተቀብለናል፡፡ ሳይጠይቁን ባህር ማዶ ተሻግረን የነሱን ባህል በማንኪያ ጨልፈን በጭላፋ እየረጨን ነው፡፡ ማንነት ክብር ሲያጣ ሰብአዊነትም ረከሰ፡፡ የሀበሻ ሞት ልክ የአንድ እንስሳ ሞት ያክል እንኳ ማስደንገጥ እያቆመ ነው (በየጊዜው በ አረብ ሃገራት የሚደርሱ ዘግናኝ አደጋዎችን ማንሳት በቂ ነው)፡፡ መከራችንና ስቃያችን የትናንት ማንነታችንን አስረሳን፡፡ አሁን አሁን ትውልዱ በ ቅኝ ከተገዙት እኩል ፈረንጂን ማምለክ ጀመረ፡፡

….በጣም የሚያሳዝነው ግን አንድ ፈረንጂ እንደዚህ ሆነ ሲባል ደረቱን የሚደቃ ሐበሻ፤ አንድ አፍሪካዊ/ ኢትዮጵያዊ እንዲህ ሆነ ሲባል የሚሰጠው መልስ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ይህ ምን ያክል ነጭ አምላኪ እንደሆንን እና ለወገን ያለን ፍቅር እየመነመነ መሄዱን ያሳያል፡፡ ይህ እንግዲህ አንዱ በእኛና በትናንት አባቶች መካከል ያለውን የትውልድ ክፍተት የሚያሳይ ነው፡፡ የአንድ ሀበሻ ደም ከሩቅ የሚከረፋቸው አባቶች በነበሩበት ኢትዮጵያ የወገኑ እንግልትና ሞት ምንም መስሎ የማይሰማው ትውልድ/ ከፍ ሲልም በወገኑ ስቃይና መከራ ላይ ቁማር የሚጫወት፣ በደማቸውና በአጥንታቸው ላይ መኖሪያውን የሚገነባ ህሊና አልባ ትውልድ መመልከት፤ የሀገርን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያንንም ተስፋ እየቀበርን ለመሆናችን ማሳያ ነው፡፡

እንግዲህ ገጣሚው “ሳንርቅ እንጠይቅ…..” እንዳለው በተሳሳተ መንገድ ረጅም ርቀት ከመጓዛችን በፊት ቆም ብለን ትክክለኛውን መንገድ ማመዛዘን ያለብን ይመስለኛል፡፡
                                                     ሻሎም!
 No comments:

Post a Comment