Monday, February 20, 2017

ከ ቢሾፍቱ ሐይቅ አፋፍ ላይ

(ከ ፕሮፌሰሩ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ)

ቢሾፍቱ ነፍስን የሚገዙ ትንንሽ ሀይቆችን በተፈጥሮ የተቸረች ምርጥ ከተማ ናት፡፡ በተደጋጋሚ ጎብኝቻታለሁ፡፡ ግን አልጠግባትም፡፡ ሐይቆቿ ነፍሴን ይገዙታል፡፡ ከ እራሴ ጋር እንዳወራ እድል ይሰጡኛል፡፡ ከ ዓለም ጫጫታ ወጥቼ ከ ማዕበሉ ጉዞ ጋር ነፍሴን አስማምቼ በምናብ እንድመጥቅ፣ ከ ሀሳቤ ህመሜ ለ አፍታም ቢሆን እንድላቀቅ ይረዱኛል፡፡ ሐይቅ እወዳለሁ፡፡ ጣና፣ ደብረዘይት፣ ዝዋይ፣ ሐዋሳ፣ ዘንገና፣ አለማያ……በተጋጋሚ ባያቸውም አልጠግባቸውም፡፡ ሁሌም ከጉያቸው ቁጭ ብዬ የሚተነፍሱትን አየር ወደ ውስጤ መማግ ያረካኛል፡፡ ንፁህ አየራቸውን ስስብ፣ አዲስ ተስፋና አዲስ ህይወት ይታየኛል፡፡ ከ ጀርባዬ ያለ ሸክም የተራገፈ ያክል ነፃነት ይሰማኛል፡፡ ጥሎብኝ ሐይቅ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮን አደንቃለሁ፡፡
ከ ቢሾፍቱ ፈርጦች ውስጥ በ ርዕሰ ከተማዋ ስም የተሰየመችው ቢሾፍቱ ሐይቅ አፋፍ ላይ ቁጭ ብዬ ከማዕበሉ ጋር በመጫወት ላይ ሳለሁ እርዳታዬን ፈልጎ አንድ አሮጌ ፈረንጂ ወደ ተቀመጥሁበት ወንበር መጣ፡፡ (እዚህ ጋ ያዝ ላድርገውና ስለ ቢሾፍቱ ሐይቅ ትንሽ ልበል፡፡)

‹‹ ……ቢሾፍቱ ሐይቅ ዙሪያዋን በሰንሰለታማ ተራራ የተከበበች፣ በከተማዋ የምዕራብ አቅጣጫ የምትገኝ ትንሽ ሐይቅ ናት፡፡ በዙሪያዋ ያለው ያገጠጠ ተራራ በደን ቢሸፈን ኑሮ አዊ ዞን ያለው ዘንገና ሐይቅ እዚህ እንዴት መጣ ያስብላል፡፡ በዙሪያዋ ያለው ተራራና ተዳፋት፣ የምትታይ እንጂ በ እጂ የማትነካ ሐይቅ አድርጓታል፡፡ በዚህም ምክንያት በሪዞርቶች የመከበብ እድልን ነፍጓታል፡፡ አልፎ አልፎ ግን ተራራውን በመቦርቦርና ወደ ሀይቁ መውረጃ በመስራት እየተገነቡ ያሉ ሆቴሎች ይታያሉ፡፡ አፋፍ ላይ ከሚገኘው ከ ቢሾፍቱ ሆቴል ተቀምጦ በመስኮት በኩል ቁልቁል ለተመለከታት አንዳች ልዩ ስሜት ይፈጥራል፡፡ ሊማሊሞን በክፍት መኪና ሳቋርጥና ጣናን በ አውሮፕላን ከላይ ወደታች ስመለከት የተሰማኝ ስሜት ከዚህም ተሰማኝ፡፡ የሆነ ደስ የሚል ስሜት!››
አሁን ወደ እንግዳዬ ልመለስ፡
Excuse me brother, can you tell me the meaning of Bajaj? አለኝ ትህትና በተሞላበት የሽማግሌ ድምፅ፡፡
No problem, I can? ....አልኩትና መረዳት በሚችልበት መልኩ ለማስረዳት ሞከርኩ (ከጎኔ የነበረ አንድ ሰው የ በውቀቱን ቀልድ አስታውሶ ‹‹በ አንቀልባ መስለህ አስረዳው›› አለኝ…….ፈገግ ብዬ…...ፈረንጂ አንቀልባ የት ያውቅና! ብዬው ወደ ማስረዳቴን ቀጠልሁ፡፡
ፈረንጁም አመስግኖኝ ወደ ቦታው ተመለሰ፡፡ ……..በአካል ላሳየው ነበር ነገር ግን ዝር የምትል ባጃጅ በአካባቢው የለችም፡፡ እድሜ ለ ጎግል፣ ምስሉን ወዲህ በል አልኩት…..በ የፈርጁ ዘረገፈልኝ…..በትህትና ለፈረንጁ አሳየሁት፡፡
በጣም አመሰገነኝና ‹‹ከየት ነው የመጣኸው፣ ስራህ ምንድን ነው›› አለኝ፡፡
(ከ አዲስ አበባ ብዬ ስራዬንና የምሰራበትን ተቋም ከነገርሁት በኋላ…..‹‹ከመጣሽ ማርያም ታምጣሽ›› ብዬ አዙሬ መጠይቅ ጀመርሁ፡፡)

(እንደወረደ ከትቤዋለሁ ተከተሉኝ…..)
እኔ፡ አንተስ ስማህ ማነው፣ ከየት ነው የመጣኸው (እዚህ ጋ የአክብሮት ቃል ያልተጠቀምሁት እንግሊዘኛውን ቀጥታ ስለተረጎምሁ መሆኑ ይሰመርልኝ)
እንግዳዬ፡ ‹‹ ጂን ሉክ እባላለሁ፡፡  የመጣሁት ፈረንሳይ ነው፡፡ በ ቦርጁን ዩኒቨርሲት የ ስነፅሁፍ ፕሮፌሰር ነኝ፡፡ በ ዚህ ዩኒቨርሲት 25 ዓመት አስተምሪያለሁ፡፡ 5 ዓመት ደግሞ የእንግሊዙ ካምብሪጅ ዪኒቨርሲቲ አስተምሪያለሁ፡፡ በጣም ብዙ ሺ ሰው የሚታደምበት በ ፈረንሳይ በየ ዓመቱ የሚካሔድ አርት ጋለሪም አዘጋጅ ነኝ፡፡››
እኔ፡ ወደ ኢትዮጵያ መችና ለምን መጣህ
ፕሮፌሰር ሉክ፡ የመጣሁት ከ አንድ ወር በፊት ነው፡፡ አሁን ጡረታ ስለወጣሁ ባለኝ ጊዜ ኢትዮጵያን እየጎበኘሁ ነው፡፡ ላሊበላን፣ አክሱምን፣ ጎንደርን፣ ጣናን፣ ኤርታሌንና ሌሎችንም ድንቅ ቦታዎችን ጎብኝቻለሁ፡፡ እዚህ (ቢሾፍቱ ለማለት ነው) የመጣሁት ትንሽ እረፍት ለማድረግ ነው፡፡
እኔ፡ ኢትዮጵያን እንዴት አገኘሃት
ፕሮፌሰር ሉክ፡ በጣም ቆንጆና ታሪካዊ ሀገር ናት፡፡ ድንቅ መስህብ ያላት ሃገር ናት፡፡ በቆይታዬ ደስተኛ ነኝ፡፡
እኔ፡ በ ኢትዮጵያ ቆይታህ ያስተዋልከው በጣም መጥፎና መልካም ነገር ምንድን ነው
ፕሮፌሰር ሉክ፡ ብዙ ጥሩ ነገር አለ፤ እኔን በጣም ያስደሰቱኝ ግን ወጣች ናቸው፡፡ 
እኔ፡ እንዴት
ፕሮፌሰር ሉክ፡ ‹‹ብዙ ወጣት አላችሁ…አንተን ጨምሮ፡፡ ወጣቶቹ ደስ ይላሉ፡፡ ፈጣን ናቸው፡፡ ታጋሽ ናቸው፡፡ ትሁት ናቸው፡፡ ያደጉ ሃገሮች የወጣት ርሃብ አጋጥሟቸዋል፡፡ ግን የእናንተ ወጣቶች ያሳዝናሉ፡፡ ብዙዎቹ ስራ የላቸውም፡፡ መንግስት ይህን ታላቅ ሃይል ለመጠቀም ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ ስራ መፍጠር አለበት፡፡ መጪው ዘመን ትንሽ የሚከብዳችሁ ይመስለኛል፡፡ በ እርግጥ ከድህነት ለመውጣት በፈተና ማለፍ ግድ ነው፡፡ ዛሬ ወደ 100 ሚለዮን የሚጠጋ ህዝብ አላችሁ፡፡ ከ 20 እና 30 አመት በኋላ የህዝብ ቁጥሩ በእጥፍ ይጨምራል፡፡ ዛሬ ጀምራችሁ በሃብታምና በድሆች መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ ካልጀመራችሁ፣ መጪው ዘመን ሊከብዳችሁ ይችላል፡፡ …….ወጣቶቹም ቢሆን በሀገራቸው መማር፣ ሰርተው መኖር ካልቻሉና የእያንዳንዱ ነገር ተጠቃሚ መሆን ካልቻሉ ወደፊት የባእዳነት/የባይተዋርነት ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለዚች ሃገር ፈተና ነው፡፡ ሌላው፤ አብዛኛው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀሰው አዲስ አበባ ላይ ነው፡፡ ይህ ክ/ሀገር አካባቢ ላሉት ወጣቶች የስራ እድል ለማግኘት ያላቸውን እድል ከባድ ያደርገዋል፡፡ ተቋማትና ፋብሪካዎች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ወደ ክልሎችም መከፈት አለባቸው፡፡ በአጠቃላይ በ አጉል ስፍራና በየጎዳናው በመጓዝ የሚባክን ታላቅ የወጣት ሃይል ታዝቤአለሁ››
እኔ፡ ኢትዮጵያ ከፈረንሳይ ምን መማር አለባት ትላለህ
ፕሮፌሰር ሉክ፡ ፈረንሳይና ሌሎች የአውሮፓ ሃገራት መሬት የረገጠ ስርዓት አላቸው፡፡ የሚመሩት በተቀመጠው ስርዓት አንጂ በግለሰቦች አይደለም፡፡ ብዙ የአፍሪካ ሃገሮች ግን ለዚህ አልታደሉም፡፡ ወደዚያ ለመምጣት ትንሽ ዋጋ ያስከፍላችኋል፡፡
እኔ፡ የፈረንሳይ ዕጩ መሪዎች ውድድር ላይ ናቸው፡፡ አንተ የማን ደጋፊ ነህ፡፡
ፕሮፌሰር ሉክ፡ እኔ አንድ እምነት አለኝ፡፡ ሀገር መምራት ያለባቸው ወጣቶች ናቸው፡፡ ወጣቶች ለ ለውጥ ፈጣን ናቸው፡፡ በእድሜ የበሰሉ ሰዎች ከጎን ሁነው ሊያማክሩና አቅጣጫ ሊያሳዩ ይችላሉ፡፡ እኔም የምደግፈው ወጣቱን ዕጩ ተፎካካሪ ነው፡፡ ምንም እንኳ የግራ ዘመም ፖለቲካ አራማጅ ቢሆንም፣ ከ እሷ (ከሴቷ ተወዳዳሪ ማለቱ ነው) የተሸለ አቅምና ብቃት አለው፡፡ ያሸንፋል ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ የእኔም ድምፅ ዋጋ ስላለው እመርጠዋለሁ፡፡
እኔ፡ በጉብኝትህ ወቅት ያየኸውን ወደ መፅሃፍ የመቀየር ሃሳብ አለህ፡፡
ፕሮፌሰር ሉክ፡ ብዙ ወደ መፅሃፍ መቀየር ያለብኝ ስራዎች አሉ፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ገና ብዙ ማንበብ አለብኝ፡፡ ሌሎች ሀገሮችንም መጎብኘት አለብኝ፡፡ ከዚያ በኋላ አላቅም፣ ልፅፍ እችላለሁ፡፡
እኔ፡ ኢትዮጵያ እሰከ መቼ ትቆያለህ፡፡
ፕሮፌሰር ሉክ፡ ከሁለት ቀን በኋላ ወደ ቱርክ እሄዳሁ፡፡ ኢስታንቡልን መጎብኘት አለብኝ፡፡ (ኢስታንቡል ኢትዮጵያውያንን ያፈዘዙት ‹‹ጥቁር ፍቅርና ቅጣት›› የተሰኙት ተከታታይ ፊልሞች የተሰሩባት፣ በተፈጥሮ በብዙ ሐይቆች የታደለች ውብ ከተማ ናት)
እኔ፡ ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ሃሳብ የለህም
ፕሮፌሰር ሉክ፡ የ ዛሬ አመት እመጣለሁ፡፡ አድራሻ እንቀያየርና ያኔ በ ሰፊው እንጫወታለን፡፡ አሁን ጓደኛህ እየጠበቀህ ነው አለኝ፡፡
(በጨዋታችን ተመስጬ አብሮኝ የነበረውን ጓደኛዬን ዘንግቸው ነበር፤ ዞር ብዬ ሳየው እሱም ከሐይቁ ጋር ቃለመጠይቅ እያደረገ ነው)
እኔ፡ በጣም አመሰግናለሁ ፕሮፌሰር፡፡ መልካማ ጊዜ ይሁንልህ!
ፕሮፌሰር ሉክ፡ እኔም ከ ልብ አመሰግናለሁ፡፡ በ ቅርቡ እፅፍልሃለሁ! ዳግም እንደምንገናኝ ተስፋ አለኝ፡፡
እኔ፡ እኔም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ 
(ፕሮፌሰር ሊቅ ነው፣ በ አንድ ወር ቆይታው የእኛን ዛሬ ገምግሞ፣ ነጋችን ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ሞክሯል፡፡ በ እርግጥ ከፈረንጂ አፍ እንስማው ካልሆነ በቀር፣ ያነሳቸው ሃሳቦች አግጠው የምናያቸው የቀን ተቀን  እውነታዎች ናቸው)፡፡     
ፕሮፌሰሩን ሞቅ ባለ የእጂ ሰላምታ፣ ቢሾፍቱን ደግሞ በመልካም ትዝታ ተሰናብቼ ወደ ሰገባዬ ተመለስሁ፡፡

አዲስ አበባ …አዲስ አበባ…… ሁለት ሰው………..!!!

1 comment:

  1. ‹‹ብዙ ወጣት አላችሁ…አንተን ጨምሮ፡፡ ወጣቶቹ ደስ ይላሉ፡፡ ፈጣን ናቸው፡፡ ታጋሽ ናቸው፡፡ ትሁት ናቸው፡፡ ያደጉ ሃገሮች የወጣት ርሃብ አጋጥሟቸዋል፡፡ ግን የእናንተ ወጣቶች ያሳዝናሉ፡፡ ብዙዎቹ ስራ የላቸውም፡፡ መንግስት ይህን ታላቅ ሃይል ለመጠቀም ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ ስራ መፍጠር አለበት፡፡ መጪው ዘመን ትንሽ የሚከብዳችሁ ይመስለኛል፡፡ በ እርግጥ ከድህነት ለመውጣት በፈተና ማለፍ ግድ ነው፡፡ ዛሬ ወደ 100 ሚለዮን የሚጠጋ ህዝብ አላችሁ፡፡ ከ 20 እና 30 አመት በኋላ የህዝብ ቁጥሩ በእጥፍ ይጨምራል፡፡ ዛሬ ጀምራችሁ በሃብታምና በድሆች መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ ካልጀመራችሁ፣ መጪው ዘመን ሊከብዳችሁ ይችላል፡፡ …….ወጣቶቹም ቢሆን በሀገራቸው መማር፣ ሰርተው መኖር ካልቻሉና የእያንዳንዱ ነገር ተጠቃሚ መሆን ካልቻሉ ወደፊት የባእዳነት/የባይተዋርነት ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለዚች ሃገር ፈተና ነው፡፡ ሌላው፤ አብዛኛው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀሰው አዲስ አበባ ላይ ነው፡፡ ይህ ክ/ሀገር አካባቢ ላሉት ወጣቶች የስራ እድል ለማግኘት ያላቸውን እድል ከባድ ያደርገዋል፡፡ ተቋማትና ፋብሪካዎች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ወደ ክልሎችም መከፈት አለባቸው፡፡ በአጠቃላይ በ አጉል ስፍራና በየጎዳናው በመጓዝ የሚባክን ታላቅ የወጣት ሃይል ታዝቤአለሁ››

    ReplyDelete