Thursday, June 22, 2017

የ ሲኦል ነፍሳት:ክፍል ፩

አዲስ አበባ ከቤቴ ይዞኝ የወጣው ሹፌር፣ በመካኒሳ በኩል አቋርጦ ወደ ፈጣን መንገዱ ገባ፡፡ ከዚያም መኪናዋን እንደ ኮሪያ ሚሳኤል ያስወነጭፋት ጀመር፡፡ ሩቅ ከሄድሁበት ሀሳብ ብንን ያልሁት ሹፌሩ የሚሰቀጥጥ ‹‹ክላክስ›› ድምፅ ሲያሰማ ነው፡፡ ፍጥነት ታጥፎ ወደ ፈጣን መንገዱ ከሚገባ መኪና ጋር ሊላተም ለትንሽ ተረፍን፡፡
ከዚህ አሰፋ መዝገቡ እለት የመኪና አደጋ ሞት ወይም አካል ጉዳት ሪፖርት የተረፍነው፣ የሌላኛዋ መኪና ሹፌር መሪውን ጠምዝዞ ከመንገዱ በመውጣቱ ነበር፡፡ መኪናዋ ትንሽ ብትጎዳም ሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አልነበረም፡፡ አዲስ ዜና አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በየቀኑ ከሚደርሱ አሰቃቂ አደጋዎች በጣም ቀላሉና ለወሬ የማይበቃ ነው፡፡ ችግሩ ግን ‹‹ የዛሬ ንጥሻ ወደ ከፋ ጉንፋን ከማደግ አይመለስም››፡፡ እኛም ስለጉንፋኑ ማውራት እንጂ ንጥሻውንና ጉንፋኑን የሚያመጡትን ነገሮች ስለመከላከል ስንደክም አይታይም፡፡

ሹፌሩ ዝግ ብሎና አስተውሎ እንዲነዳ ቁጣ አዘል ምክር ማሰጠንቀቂያ ጋር አዋጠን ለገስነው፡፡ ምክራችንን የተቀበለ መሆኑን ለማሳየት የተወሰነ ደቂቃ ረጋ ብሎ ነዳ፡፡ ከዚያ አመሉ መጣበት….‹‹አባሰው!›› አሉ እኒያ ሴትዮ ወደው ነው!
ድንጋጤው መልስ አንድ ጓደኛችን ጣቱን ወደ ውጭ እየጠቆመ..... ‹‹አያችሁ ከዚያ ወዲያ የምታዩት እኮ እስር ቤት ማስፋፋፊያ ነው›› አለ
አንደኛውም ጎን ተቀብሎ …‹‹ ደንብ አስበውበታል ግን››
‹‹ምኑን›› አለ ተቀበለና
‹‹…..90 ሚሊዮን ሰው ይችላል›› ሲል ጠየቀ፡፡ ሁላችንም በቆሎ ፈገግታ ታጀብን!
እንዲህና እንዲህ እያልን የሆዳችንን ሳይሆን አፋችንን እያወራን ወቢቷን ደብረዘይትን ሹፈናት አለፍን፡፡ ማን የልቡን ያወራል ወዳጄ፣ እሱ ድሮ ቀረ!

………መልካም ነገርን ሁሉ ድሮ ጋር የማቆራኘት አባዜ እንዳለብን ባውቅም ‹‹አብዛኛው ሰው የጨጓራ በሽተኛና መሸተኛ›› የሆነው የልቡን ከሰው ጋር ስለማያወራ ነው፡፡ ‹‹ አንድ ላይ ብንሆንም ተለያይተናል›› እንዲል ከያኒው ሰው ከሰው ርቋል፡፡ ሰው ሰው ደበቀውን ሚስጢርና ውስጡን እውነት ብርጭቆ ከንፈር ሲያወራ ያመሻል፡፡ ማመንና መተማመን፣ መናገርና መነጋገር፣ ማሰብና መተሳሰብ ሲነጥፍ፣< እውነቱ ወደ ህመም ቃላቶቹ ወደ ሙዚዬም> ተቀየሩ፡፡
ሰዓታት በኋላ እራሴን ደቡብ ምስራቋ ፈርጥ አዳማ ከተማ ውስጥ አገኘሁት፡፡ ጥሎብኝ አዳማን እወደታለሁ፡፡ አንዳዴ ደግሞ እጠላታለሁ፡፡ ወከባዋ ይረብሸኛል፡፡ እርግጥ አዲስ አበባ አይብስም፡፡ አዳማ ሌላኛዋ ትንሽየዋ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ቀን ትንሽ ሙቀቷ ቢረብሽም መሸት ሲል ግን አየሯ አጅን ዘርግተው የሚመገቡት መና ነው፡፡ ሲመሽ አየሯ ብቻ ሳይሆን ቆንጆቿም በዓታቸው እየወጡ ከተሜው ውበታቸውን ያፈሳሉ፡፡ ከባርና ከሆቴሎች የሚረጩ መብራቶችና ዲምላይቶች አንድን ሰው አራት አምስት ውበት ያስገበኛሉ፡፡ ዚያው መጠን ቆንጆዎቹ ለተመልካች በዝተው ይታያሉ፡፡

ብቻዬን ነኝ፡፡ ከብቸነት ጭቅጭቅ ለመሸሽ እግሬ ‹‹ኤክስኩቲቭ›› ሆቴል ተንስቼ ወደ መሃል ከተማ ማዝገም ጀመርሁ፡፡
ነገራችን ላይ አውራ ጎዳና እስከ ፖስታ ቤት መንገዱ ዳር የተኮለኮሉ አዳማ ከተማ ሆቴሎችን ስም ያስተዋለ፣ ‹‹አዳማ እንግሊዞች ቅኝ ግዛት ስር ነበረች እንዴ›› ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ‹‹ኤክስኩቲቭ›› ‹‹ሪፍት ቫሊ›› ‹‹ኮምፎርት›› የመሳሰሉትን ማንሳት ይቻላል፡፡
እዚች ላይ አንድ እንግሊዝኛ ቋንቋ ጋር የግል ጠብ ያለበት አንድ ካድሬ አንድ ወቅት የሆቴሎን ስም ጓደኛው ለማስረዳት የገጠመውን ፈተና አንስተን እንለፍ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው
‹‹አንድ ስብሰባ ኤክስኩቲቭ ሆቴል ውስጥ ይጠራል፡፡ አርፍዶ ወደ ስብሰባው የመጣ አንድ ተሰብሳቢ ቀድሞ ወደ ደረሰ ጓደኛው ደውሎ የስብሰባውን ትክክለኛ ቦታ ይጠይቀዋል፡፡ ጓዱም በሚችለው መጠን የሆቴሉን ስም እየጠራ ሊያስረዳው ይሞክራል፡፡ ነገር ግን ‹‹ኤክስኩቲቭ›› የሚለውን ቃል በትክክል መጥራት ይከብደዋልከዚያም ወደ አማርኛ ተርጉሞ ለመናገር ይሞክራል፡፡ አስቦ አልቀረም ወዲያ ጉጉት ሚጠብቀው ሰው ‹‹ ዋና አለቃ ሆቴል ነው ያለነው›› ሲል ያስረዳዋል፡፡ ሰውዬው የበለጠ ግራ ይጋባል…..ከዚያም ከጎኑ የነበረ ጓደኛው ስልኩን ተቀብሎ ገላገለው፡፡››
…….ምን ይደረግ እንግዲለጥሪም ለትርጉምም የሚያስቸግር ስም የትልቅነት መለኪያ ከሆነ ሰነበተ መሰለኝ፡፡ ይህን ስል ሀገርኛ ስም የኮሩ እነ ‹‹ቶኩማ፣ ድሬና ዳሎል›› የመሳሰሉትን ማሞገሱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ! ………እንዲህና እንዲህ እያልሁ ሀሳቤን እያመነዠክሁ፣ሒሳቤን አልፎ ሂያጅ እየጠበቅሁ፣ መለስ ቀለስ እያልሁ የምሽት ትርዒቶቿን እቃኛለሁ፡፡ እዚህ ሁሉም ነገር በፍጥነት ይከናወናል፡፡ ሰው በፍትነት ታክሲ ያሳፈራል፣ በፍጥነት ይጓዛል፣ በፍጥነት ይሳሳማል፣ በፍጥነት ይበላል፣ በፍጥነት ይጠጣል፣ በፍጥነት ያወራል……ዳግም ምፃት የሚመጣው አዳማ ከተማ ብቻ ይመስል ሁሉም ነገር በፍጥነት ይደረጋል፡፡
መንገዱ ዳር ሁለቱም አቅጣጫ ‹‹ኮንደምና ሲጋራ›› የሚሸጡ ወጣቶችና ህፃናት ተኮልኩለዋል፡፡ እስከማውቀው ድረስ መንገድ ዳር ኮንደም በይፋ የሚሸጥባት ከተማ አዳማ ናት፡፡ አዳማ ወሲብ ለብዙ እንስቶች ብቻ ሳይሆን ብዙ ህጻናት የስራ እድል የፈጠረ እርኩስ ተግባር ነው ብሎ መፃፍ ይቻላል፡፡ ግን አንድ ነገር ጥሩም መጥፎም የሚሆነው ንፅፅር ነው፡፡ ህፃናት ህይወት በማይገደው ዓለም ውስጥ፣ እነዚህ ህፃናት ስራ እርኩስ ተግባር ነው ብሎ ማብጠልጠል እጂ የያዙትን ዳቦ ቀምቶ እንደ መርገጥ ይቆጠራል፡፡
እኔም ወደ አንዱ ህፃን ልጅ ጠጋ አልኩ፡፡ ከዚያ 3 ብር አውጥቼ ማስቲካ ገዛሁ (ሃሃሃሃሃ……እና ምን መስሏችሁ ነው)፡፡
ፖስታ ቤት አካባቢ ስደርስ ወደ ግራ ታጥፌ ወደ ‹‹ገደል ግቡ ሰፈር›› አመራሁ፡፡ (አንባቢ ሆይ ‹‹ገደል ግቡ›› የሚባለው ሰፈር ራቀ ያለ ቢሆንም ዛሬ ግን ሆስፒታሉ አካባቢ ያሉት በተራ የተኮለኮሉ ምሽት ቤቶች እኔ ‹‹ገደል ግቡ ሰፈር›› እንደሆኑ አስበህ አንብብልኝ››………….
ልቀጠል! ገደል ግቡ ሰፈር ደምቃለች፡፡ በዲምላይት ደመቁ ጭፈራ ቤቶች በር ላይ ደመ-ግቡ ቆነጃጅት ውር ውር ይላሉ፡፡ እንደ ሳት ራት ብቅ ብለው ይጠፋሉ፡፡ አሁንም በር ላይ ውልብ ብለው ይጠፋሉ፡፡ ይህን ሳይ ዓለም ቁጥር አንዱ ቢሊዬነር ‹‹ቢልጌት›› ላይ አንድ ወቅት የተቀለደው ቀልድ ትዝ አለኝ፡፡
‹‹አንድ ቀን ቢልጌት ሞተ አሉ፡፡ ላሳጥረው! መላዕክት ነፍሱን አጅበው ለፍርድ ይዘዋት ሄዱ (ኢትዮጵያ በመጣ ጊዜ አጅበውት የነበሩት 7 ጋርዶች አብረው አልነበሩም)፡፡ ከዚም ምርጫ አቀረቡለት፡፡ ገነትን አሳዩት፡፡ ነጭ የለበሱ ሰዎች የሞሉት፣ ፀሎትና ምስጋና የበዛበት አርምሞ ቦታ ነው፡፡ ሲኦልን አሳዩት፡፡ ቆነጃጅት የበዙበት፣ ጭፈራና ዳንኪራ የበዛበት ቦታ ነው፡፡ አሁን ምረጥ አሉት፡፡ ቢሊየነሩ ሲኦልን መረጠ፡፡ ከዚያ መላዕክት አጅበው ወደ ሲኦል ወሰዱት፡፡ ነገር ግን ሲኦል ሲገባ ቅድም ያያቸው ቆነጃጅት አልነበሩም፡፡ ይልቁንስ እንደ ቁራ ጠቁረው፣ ጥላሸትን አጎፍረው ተመለከተ፡፡ ወደዚያ የወሰዱትን መላዕክት…. ቅድም ያሳያችሁኝ ቆነጃጅት የት አሉ ብሎ ጠየቀ፡፡ አንደኛው መላክ እነሱማ ‹‹እስክሪን ሴቨር ናቸው›› ብሎ መለሰለት ይባላል፡፡››
ይህች ወቅቱ የቢልጌትን ‹‹ማይክሮሶፍት›› ፈጣሪነት አስመልክቶ የተቀለደች ቀልድ ብትሆንም ለእኔ ግን የማያቸው እንስቶች ሁሉ እንደ ስክሪን ሴቨር ውልብ ብለው ይጠፋሉ፡፡ ስክሪን ሴቨር አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ ቀርቦ ማዬት ግድ ይላል፡፡

ተወዛገበና! ተወዛገበና! ወንድ ልጅ ቆረጠ፡፡ ለማንኛውም የምሄደው ወደ ሰማይ ሲኦል ይሁን ወደ ምድራዊው ባላውቅም አንደኛው ጭፈራ ቤት ታዛ ስር ደርሻለሁ፡፡ በር አካባቢ የነበረችው አንዲት ቆንጆ በዳሌዋ ገርምማኝ፣ በአይኖቿ አጩላኝ በሩን ከፍታ ገባች፡፡ በሩን የመክፈቷ ቅኔ ጭንቅላቴን ጠቅ አረገኝ፡፡ ‹‹ቢልጌት›› ተረት እያሰብሁ ወደ ውስጥ መግባት ፈራሁ፡፡ ማቅማማቴን ያነበበው የምሽት ቤቱ ዘበኛ ግባ በሚል የግዳጅ ፈግግታ ታጅቦ ሁለት እጁን ዘረጋልኝ፡፡

ይህ ሰው ‹‹ነፍሳትን ወደ መረቡ የሚያስገባ የሲኦል ዘበኛ›› መስሎ ተሰማኝ፡፡ ወንድ ልጅ ፈርቶ አይሞትም ለራሴ ፈከርኩ፡፡ የልብ ትርታዬ ጨምሯል! ወደ ውስጥ ገባሁ፡፡ 14 ያፈጠጡ አይኖች ሁሉም በአንድ ጊዜ ወደ እኔ አማተሩ፡፡ በጣም ደነገጥሁ፡፡ እንደፈረደብኝ መደነባበር ጀመርሁ፡፡
ይቀጥላል!………

#ማሳሰቢያ 
አቢሲንያ መዝገበ ቃላት ያኘሁት እንዲህ ይላል፡፡
1) ‹‹
ነፍስ›› ለሚለው ቃል ብዙ ቃሉ ግዕዝ ‹‹ ነፍሳት›› ሲለው አማርኛ ደግሞ ‹‹ነፍሶች›› ይለዋል፡፡
2)
ምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ትንንሽ ፍጥረታትን አማርኛው ነጠላ‹‹ ነፍሳት›› ብሎ ይጠራቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ብዙ ቁጥር ሲቀየር ‹‹ነፍሳቶች›› ይሆናል፡፡ እኔም ፅሁፍ ‹‹ነፍስ›› ላይ ሳይሆን…. ተፀውኦ ስም ‹‹ነፍሳቶች›› ላይ ያተኮረ ነው፡፡ 
(
የሰዋሰው ግድፈት ያለ እንዳይመስላችሁ በዚህ ተረዱልኝ፡፡
) 


No comments:

Post a Comment