Monday, June 19, 2017

እነሆ በ ክረምት-የቅኔ በረከት


በውቀቱ የ‹‹ኦሾ›› መፅሃፍ ከ እምነቱ ሳይሆን ከ ሃይማኖቱ እንዳቆራረጠው ‹‹ ከ አሜን ባሻገር›› ላይ ሹክ ብሎን ነበር፡፡ ምን አልባት በውቄ የ ‹‹ Der Antichrist›› ፀሐፊ የሆነውን የ ጀርመኑን ‹‹ፍሬዲሪክ ኒቼ››ን እጣ ፈንታ ካነበበ በኋላ ሃሳቡን የቀየረ መሰለኝ፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ከሁሉም በላይ የቀደመ ሃይማኖቱ ‹‹የማለዳ ድባብ›› ከተኛበት ቀስቀሶ፣ ከሄደበት መልሶ፣ የቅኔ ጣእሩን አስተንፍሶ ለመድብሉ የወል ስም እንዲሆን ያሰገደደው፡፡ በ ቆመበት ማን ይኖራል! በውቀቱ ገጣሚ መሆኑ ብቻ ሳይሆን እይታው በጣም ይገርመኛል፡፡ ለማኛውም እምነትህ የራስህ ነው፣ ግጥምህን በ ቶሎ ወዲህ በል!….ከፈለግህ በ ‹‹ኦሾ››…አሊያም በ‹‹ኒቼ›› ማመን ትችላህ፡፡ አይመለከተኝም! ይችን ነገር ልጠቀም መሰለኝ (lol)

አለ እንጂ ደግሞ ያ በላይ በቀለ ‹‹አንቅልፍ እና ሴት›› የሚለውን ክሽን ግጥም ሸበሌ መርቀን አጣጥመን ዓመት ሳይሞላን ‹‹ከ ሴተኛ አዳሪ የተኮረጀ ሳቅ›› ብሎ ሊያስቀን ይሁን ሊያሳቅቀን ከተፍ ብሏል፡፡  ይህ ብላቴና የራሱ የሆነ ድንቅ እይታና የ ግጥም ቆጠራ ዘዴ ያለው ልጅ ነው፡፡ ‹‹መልሱን ጠጣሁበት››፣ ‹‹እንቅስቃሴዎች ሁሉ ፖለቲካ ናቸው›› በጣም የመሰጡኝ ግጥሞች ናቸው፡፡ የግጥም ከራማው ይጠብቅህ!

የሰው ልጅ ከ ‹‹ብረት ነፍጥ›› ወደ ‹‹ሀሳብ ነፍጥ›› መሸጋገር እንዳለበት በማመን፣ በ መለኛ ሀሳቦቹ ሲሞግተን ከርሞ የ ሀሳብ ነፍጥ ባነገቡ ‹‹ነፍጠኛ ስንኞች›› ከተፍ ያለው መላኩ ‹‹ከፍ ገር - ዝቅ በዘር›› የሚል ቅምሻ ወርውሮ ጉጉት ረሃብ እየቆላን ነው፡፡ ‹‹የሚያጠግብ እንጀራ…›› እንዲሉ መሌ በብዙ የሚጠበቅ ብላቴና ነው፡፡

የት አል ደግሞ ያ አድፍጦ አስደማሚ ስንኞችን የሚያስወነጭፈው ፍቃዱ ጌታቸው፡፡ በ ገፃቸው ሄጀ ምን እንደፃፉ ከ ምጎበኛቸው ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ፍቄ ‹‹ማር የመሆን ዜማ››ን ማር በሆኑ ቃላቶች ከትቦ ከተፍ ብሏል፡፡ ፍቄ በ አንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፡፡
‹‹እምዬ ኢትዮጵያ  አንቺ ትልቅ ዛፍ
ሁሉ እየተነሳ ግንድ ነኝ እያለ ሌላው ቅርንጫፍ
በሞቴ ንገሪኝ የቱጋ  ልረፍ
?››
አቦ አሁንስ እኛም ማረፍ እንፈልጋለን፡፡ ፈጥናችሁ አንዳችሁ ጀባ በሉንና የ ክረምቱን መግቢያ እናሟሙቅ!
ለ አንባብያን ደግሞ ‹‹እነሆ በ ክረምት-የቅኔ በረከት›› ብያለሁ!

1 comment:

  1. Hello Zele, found this google.
    http://ethiopianchurch.org/en/books_reviews/297-%E1%8B%A8%E1%88%9B%E1%88%88%E1%8B%B3-%E1%8B%B5%E1%89%A3%E1%89%A5.html

    ReplyDelete