Saturday, June 24, 2017

የ ሲኦል ነፍሳት: ክፍል ፪

አቤት የሰው ዓይን ንደዚህ ያስፈራል? ዓይን የሌለበት አካባቢ ስፈልግ-ኮርነር ጋር አንድ ወንበር አገኘሁ፡፡ በፍጥነት ወደዚያ ሄጄ ተቀመጥሁ፡፡ አስተናጋጁ ገና ወንበሩ ላይ ሳልቀመጥ እየተንደረደረ መጦ ምን ልታዘዝ አለኝ፡፡ 
ቢራ አልኩት፡፡ 
‹‹
ምን ቢራ ይሁንልህ››….
የተገኘውን ብዬ መለስኩለት፡፡ 
ፍራት ውስጤን ሲያርደው ይሰማኛል፡፡ ትንሽ ቀና ስል ስገባ ያፈጠጠብኝ 7 እንስቶች 14 ዓይን አሁንም እኔ ላይ አፍጧል፡፡ መልሼ አቀረቀርሁ፡፡ ቢራው መጣ፡፡ ቀና ላለማለት ቢራውን ደጋግሜ ወደ አፌ መላክ ጀመርሁ፡፡ ድፍረት እየተሰማኝ ሲመጣ ቀና አልሁ፡፡ እኔ ውጭ ምንም አይነት ተስተናጋጅ የለም፡፡ ወዲያ የመጠጥ መደርደሪያ ይታያል፡፡ ከጎን ዲጄው የፍስክ ዘፈኖችን ወደ አየሩ ያስወነጭፋል፡፡ ጀርባ በር አካባቢ ሁለት አስተናጋጆች በተጠንቀቅ ቁመዋል፡፡ ቤቱ እኩል እርቀት 7 እንስቶች ባለጌ ወንበር ላይ ቁጭ ብለው ይቁለጨለጫሉ፡፡ አብዛኞቹ ጡታቸው ገና በአግባቡ ያላጎጠጎጠ፣ እድሜአቸው 18 ያልረገጠ ብላቴናዎች መሆናቸውን ቦግ እልም እያለ የሚያሳያቸው ዲምላይት ብርሃን ያሳብቃል፡፡…..እኒህ እንስቶች፣ ‹‹ሲኦልም ድንበር አለ እንዴ?›› በሚያሰኝ መልኩ ቦታውን እኩል የተከፋፈሉ ይመስላል፡፡

ዓይናቸውን ቀና ብዬ ማየት አለመቻሌ አንድ 10 ክፍል ጓደኛዬን ድርጊት አስታወሰኝና ከፍርሃቴ ለመውጣት ለራሴ ፈገግ አልሁኝ፡፡ ነገሩ አንዲህ ነው፡፡
‹‹ 10 ክፍል ተማሪዎች በነበርንበት ወቅት 9 ክፍል ተማሪዎች ‹‹ቲቶሪያል›› ትምህርት እንድንሰጥ ተመረጥን፡፡ ከዚያም በየ ክፍሉ (ሴክሽን) ተመደበን ወደ ክፍል ገባን፡፡ ሁላችንም አስተምረን ወጣን፡፡ አንድ ጓደኛችን ግን ለማሰተማር ገና በሩን ከፍቶ ሲገባ 60 አካባቢ የሚሆኑ ተማሪዎች ሁሉም እሱ ላይ አፈጠጡ፡፡ ጓደኛችን ‹‹ሽፌ›› ይህን መቋቋም አቃተውና የያዘውን መፅሐፍ ጥሎ በሩን ከፍቶ እየሮጠ ወጣ፡፡ ዚያም ልጁን አገኘነውና ጠየቅነው፡፡
‹‹
ሽፌ›› ምን ተፈጠረ? ….. ምን ሆነህ ነው? አልነው፡፡
‹‹ አቤት እራሳቸው ብዛቱ……………አቤት ዓይናቸው ሲያስፈራ………›› ብሎ የመለሰልን ትዝ አለኝ፡፡
እውነት ነው! የሰው ፊት በጣም ያስፈራል፡፡ ሁሉም ወደ እኔ ያፈጣሉ፡፡ አሁን ትንሽ ሞቅ ሲለኝ፣ እኔም አፀፋው ወደ እነሱ ማፍጠጥ ጀምሬአለሁ፡፡
መሃል አንዷ ትነሳና በማስቲካዋ እያፏጨች፣ ዳሌዋን የባለጌ ጨዋታ እያጫወተች ወደ በር ትሄዳለች፡፡ ወጣ ትልና ተመልሳ ትመጣለች፡፡ ዳሌዋና በእይታዋ ገላምጣኝ ባለጌ ወንበር ላይ እግሮቿን ከፍታ ትቀመጣለች፡፡ ሁሉም በየተራ እንደዚህ ያደርጋሉ፡፡ ብቻዬን ኮርነር ላይ ቁጭ ብዬ በዳኝነትም በታዳሚነትም የሚደረገውን ‹‹ፋሽን ሾው›› የመሰለ ትርኢት አከታተላለሁ፡፡ እራሴን በዳኝነት መንበር ሰይሜ ድርጊታቸውን አወዳድራለሁ፡፡ በየመሃሉ ስልክ ያላቸው ስልካቸውን ይነካካሉ፡፡ አንዳንዶች ከጎናቸው ወደ ተቀመጡት ሄደው ይንሾካሾካሉ፡፡ እኔን ለማረድ የተስማሙ እየመሰለኝ ልቤ ድጭ ድጭ ይላል፡፡ ቢራ ደጋገምሁ፡፡ 
ከመገላመጥና ማስጎምጀት ባለፈ ደፍራ ወደ ተቀመጥሁበት የመጣች እንስት እስካሁን የለችም፡፡ አዳማ አየር ጋር ተደማምሮ ቤቱን የእሳት ወላፈን ገረፈው፡፡ ስገባ የነበረው ብርክ አሁን ጥሎኝ ጠፋ፡፡ በምትኩ ሰውነቴ በወሰድሁት አልኮልና በተረጨው ወላፈን መሞቅ ጀምሯል፡፡ ነፍሴ ስጋዬ ጋር ጥል መጀመሯ ይሰማኛል፡፡ የቤቱ መሞቅ፣ ነፍሴ ከተማዋ እንደ ‹‹ሰዶምና ገሞራ›› ተቃጠለች እንዴ ብላ እንድጠይቅ አድርጓታል፡፡
ነፍሴ ተው ውጣ ትለኛለች፡፡ ስጋዬ ደግሞ ችግር የለም፣ ‹‹ክርስቶስ ለኃጥአን እንጂ ለፃድቃን አልመጣም›› ብላ ታፀናናታለች-‹‹ወዘኩሉ ዘስጋ ወዘኩላ ዘነፍስ›› እንዲል መፅሀፋ፡፡ ነፍስም እንዳይከፋት፣ ስጋም እንዳይከፋት ማለት ነው፡፡ ‹‹ሰይጣን ላመሉ መጽሀፍ ቅዱስ ይጠቅሳል›› አሉ፡፡ የእኔም ጥቅስ ከዚህ አይለይም፡፡
በነፍስና ስጋዬ ክርክር ስባዘን፣ ሁለት ጎረምሶች በሩን በርገደው ገቡ፡፡ ዙሪያ ገባውን ቃኝተው ተመልሰው ወጡ፡፡ ተከትያቸው ብወጣ በወደድሁ፣ ግን ሂሳብ መክፈል ነበረብኝ፡፡
በዚህ መሃል እንደኛዋ እንስት ባለጌ ወንበሩ ጎን ቁማ ተራ በተራ በሁለቱ ዳሌወቿ በጥፊ ታልሰኝ ጀመር፡፡ ከዚያም ወገቧን እንደ እንዝር ካሾረችው በኋላ ወንበሩ ላይ ወጣ ፊት ለፊት ተቀመጠች፡፡ እንደ ጉሙዝ ጦር የተወደሩት ጡቶቿና የተከፋፈቱት ጭኖቿ አንድ አይነት ዜማ አይኖቿ ጋር አይኖቼን ይለማመጣሉ፡፡ 
ስጋዬ ለነፍሴ አንድ ጥቅስ ጠቀሰች……..‹‹ተርቤ አላበላችሁኝም፣ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም›› በሚለው ህግ እንዳትቀጭ ተይ አንቺ ‹‹ስጋ›› አለቻት፡፡ ‹‹ማነው ረሃብን ዳቦ ጋር ብቻ ያገናኘው፡፡ ማነው ጥማትን ውሃ ጋር ብቻ ያገናኘው፡፡›› ስጋዬ ከነፍሴ መልስ አልጠበቀችም፡፡ በእጆቼ ጠቀስኋት፡፡ አስተናጋጁ ቂጧ ወንበር ሳይነካ ቢራ ታዘዛት፡፡ ፈጣሪ ይባርክሽ፡፡ ውስኪ ብትልስ ኑሮ ምን ይውጠኝ ነበር? እንዳዘንሁላት አዘነችልኝ፡፡
ቀና ብዬ ሌሎችን ስመለከት ቅናት ቢጤ የፊታቸውን ገፅ አመዳይ አስመስሎታል፡፡ አሳዘኑኝ፡፡ አንድ ፀሎት አደረስሁ……….. ‹‹አቤቱ ጌታ ሆይ የምድር እንስቶች በዚህ ቤት በዝተዋልና ለዛሬ ብቻ ወንዶችን አብዛልን››…………...ይህን ፀሎት ያደረስሁት እነሱ በማዘን ይሁን፣ ሰላም አያስወጡኝም በሚል ፍራቻ ስሜቱ ለእኔም ግልፅ አይደለም፡፡
ጠጭ አልኋት፡፡ መቅፅበት ጠርሙሱን ቢራ ባዶውን አስቀረችው፡፡ አረ አጨካከን! ቢራው ወደ ውስጧ ገብቶ ብሶቷን ሲያስታግስ፣ ምትኩ ጠርሙሱ ውስጥ ከውስጧ የወጣ አንዳች ብሶት ይታየኛል፡፡ ቢራ ደገመች፡፡ ‹‹እሁሁሁ………..›› የሚል ድምፅ ሳታስበው አሰማች፡፡
እንተዋወቅ አልኋት፡፡ በነገራችን ላይ እኔ ዓይነ አፋር ነኝ (ሃሃሃሃሃ……)፡፡ ባር ውስጥ የገባሁት ከሃዋሳ ቀጥሎ ህይወቴ ለሁለተኛ ጊዜ ቢሆንም እንስት (ባርሌዲይ) ጋብዤ ሳወራ ግን የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ስሜን ነገርኋት፡፡
‹‹ማሪያና እባላለሁ›› አለችኝ፡፡ 
ትክክለኛ ስሟ እንደማይሆን ገመትሁ፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የምጠይቃት ጥያቄ ስላጣሁ፣ ጣራ ጣራውን እያየሁ የዲምላይቱን ሪትም መቁጠር ጀመርሁ፡፡ ‹‹ኑሮ እንዴት ነው አይባል፣ ጤና እንዴት ነው አይባል፣ ስራ እንዴት ነው አይባል፣ ምን ብዬ ልጠይቅ፡፡›› በመሃላችን ያለውን የዝምታ ድባብ ለመግፈፍ፣ ‹‹በጣም ቆንጆ ነሽ›› አልኳት፡፡
‹‹አመሰግናለሁ›› አለችኝ፡፡
አንተ ደግሞ በጣም አስቀያሚ ነህ ትለኛለች ብዬ ነበር፣ ግን አላለችም፡፡ እንጀራ ነውና!
ማሪያና በዚያ ጨለማ ድባብ ውስጥ እንኳን የሚያስደነግጥ ውበት አላት፡፡ ያለማጋነን ሞናሊዛዊ ውበት የተላበሰች እንስት ናት፡፡ የሚያምር ቅንድብ የተደገፉ ውብ አይኖቿ፣ ሰልካካ አፍንጫዋ፣ ዞማ ፀጉሯ፣ አይነ ግቡ አከናፍሯ፣ ክብ ፊቷና ሰልካካ አንገቷ፤ የተመልካችን ልብ ያባባሉ፣ ባለቅኔን ለመወድስ ቃላት ያስምጣሉ፡፡ እንደ ሰሜን ተራሮች ሽቅብ የተወደሩ ጡቶቿ፣ እንኳን አልኮል የቀመሰን ሰው ቀርቶ ሱባኤ ላይ ያለን ሰው ልብ ያሸብራሉ፡፡ አንዳዴ ውበትን ለመግለፅ ቃላት ሽባ ናቸው፡፡ ከገለፅሁት በላይ ማሪያና ውብ ናት፡፡ ውጯ እንደዚህ ይመር እንጂ ውስጧን የምታውቀው እሷ ብቻ ናት፡፡
‹‹ማሪያና›› አልኳት፡፡
….‹‹አቤት›› አለች፡፡
እዚህ ህይወት ውስጥ ገባሽ ስንት አመትሽ ነው አልኋት?
‹‹እንደዚህ አይነት ጥያቄ አትጠይቀኝዘመኔን ቀናትና አመታት መቁጠር አቁሜአለሁ›› አለችኝ፡፡
ደንግጥ ብዬ ይቅርታ ጠየቅኋት፡፡ የፊቷን መቀያየር ስመለከት አንዳች ብሶት ከውስጧ ሲያቃጥላት ይታየኛል፡፡ ውስጧ የተነሳውን እሳት ነበልባል ለማጥፋት በሚመስል መልኩ ከጎኗ ያለውን ቢራ አንስታ አንድ ትንፋሽ ጨለጠችው፡፡ 
ከተወሰኑ ደቂቃዎች ዝምታ በኋላ አንድ ጥያቄ አቀርብሁላት፡፡ አብረሽኝ ትሄጃለሽ አልኋት፡፡
‹‹ዋጋ እንስማማ›› አለችኝ፡፡
ስንት ነው?
‹‹300 ብር››
አልተደራደርሁም……….እሺ….አልኋትና መጠጡን ሂሳብ ከፍዬ አንደኛው ሲኦል ወጣሁ፡፡
ግን ሲኦል የት ነው? ሂሳብ ከፍዬ ማሪያና ጋር እየወጣሁ፣ እራሴ እንዲህ ስል ተፈላሰፍሁ፡
‹‹ የኃጢአትን ቦታ ጭፈራ ቤትና መጠጥ ቤት ያደረገው ማን ነው?……..ሲኦልን ቦታ የከለለው ማን ነው?…… መሸታ ቤት በር የተገኘን ሁሉ ኃጥዕ፣ ደጀ ሰላም በር የተገኘን ሁሉ ፃድቅ ያደረገው ማነው?………….ማንም፡፡ ሲኦል ያለው በሰው ልብ እንጂ በቦታ አይደለም………..››
ይቀጥላል!


No comments:

Post a Comment