Monday, August 13, 2018

‹‹ፍቅር›› ወይስ ‹‹ፍትህ›› የትኛው ይቀድማል?



ሰልጥነናል፣ ደሞክርሰናል፣ አድገናል እንላለን እንጂ ቁልቁል እየተምዘገዘግን ነው፡፡ ለአንድ ማህበረሰብ የእድገትም ይሁን የስልጣኔ መሰረት ለዘመናት ያካበተው የአስተሳሰብ፣ የሀይማኖት፣ የባህል እና የሞራል እሴት ነው፡፡ ይህ እሴት በዘመን መንገድ ውስጥ ተናደ፡፡ የ60ዎች ትውልድ በማህበረሰቡ ውስጥ የነበሩ የመተማመን ድልድዮችን ሰብረው፣ የመጠራጠርን ግንብ ሰሩ፡፡ በ60ዎች ከተፈለፈሉት የመደብ ተጋዮች በህይወት ተርፎ በትረ መንግስቱን የጨበጠው ‹‹ትህነግ›› የተራረፉ ድልድዮችን ሰባበራቸው፡፡ አንዱ አንዱን በአይነቁራኛ መከታል ጀመረ፡፡ አጥሩ እየጠነከረ ሂዶ ዘመን በሚሻገር የዘር አጥር ታጠረ፡፡ ትህነግ ‹‹ ንግበር በአርያነ…..›› ብሎ የፈጠራቸው የየብሔሩ ድርጅቶችም ድልድይ አፍርሶ ግድግዳ መጠገን ላይ ተጠመዱ፡፡
ትውልድ ከእናቱ ጡት እና በመከራ ከተገኘ ዳቦ ጋር የጥላቻ ውስኪ እየጠጣ አደገ፡፡ በእልህና በጥላቻ ሰከረ፡፡ ጭላንጭል ነፃነት ስትገኝ ሁሉም የጥላቻ ቅርሻቱን መትፋት ጀመረ፡፡ ሻሸመኔ፣ ጅግጅጋ፣ ሀዋሳ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ እና መሰል ቦታዎች ያየነው ድርጊት በወራት ተረግዞ በቀናት ውስጥ የተወለደ ሾተላይ አይደለም፡፡ ብዙ  አስርት ዓመታት የተረገዘ ፅንስ ነው፡፡ አጋጣሚዎች ሲገኙ ይህ የጥላቻ ፅንስ ይወለዳል፡፡ ከሰውነት ባህርይ ውስጥ ‹‹እንስሳዊ›› ባህርይ ጎልቶ ይወጣል፡፡ የ‹‹ህግ የበላይነት›› የቡድን ሲሆን፣ ሰው ህግ አፍራሽ እንጂ ህግ አክባሪ መሆን ተነሳው፡፡ በ‹‹ህግ አምላክ›› ሲባል ከቆመበት የማይንቀሳቀስ ማህበረሰብ ከፖሊስ እና ከመከላከያ ጋር የሚተናነቅ ትውልድ ፈጠረ፡፡ በ‹‹ህዝብ የማይታመን የመንግስት ስርዓት›› የማይተማመን ትውልድ እና የማይታመን የፍትህ አካል ፈጠረ፡፡ 


ችግሩ ዘርፈ ብዙ እንደመሆኑ መጠን፣ መፍትሔውም ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ሀገራዊ መግባባትን እና መተማመንን ‹‹እንደመር›› በማለት እና ‹‹ስለ ፍቅር›› በማቀንቀን ብቻ ማምጣት አይቻልም፡፡ ‹‹አንዱ እየበላ፣ እንዱ በሚያለቅስባት፤ አንዱ እየገደለ፣ አንዱ እየተገደለ በሚኖርባት ምድር ‹‹ፍቅር›› ሳይሆን ‹‹ፍትህ›› ይቀድማል፡፡ ሰው በ‹‹በፍቅር›› እንዲኖር ‹‹ፍትህ›› ያስፈልጋል፡፡

ማጣፊያው እንዲያጥር እና ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ እንደትወጣ ብሎም ወደ ዲሞክራሲ እንደትሸጋገር አንድ ነገር መሰራት አለበት፡፡ እሱም ‹‹ የህዝብ ስርዓት›› መመስረት ነው፡፡ ከፖለቲካ፣ ከዘር እና ከሐይማኖት ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ‹‹የህዝብ ስርዓት››! ነፃና እና ሀገራዊ የሆነ ሚዲያ፣ የፍትህ መስሪያ ቤት፣ የደህንነት መስሪያ ቤት፣ ምርጫ ቦርድ፣ ዩኒቨርሲቲ፣ ጉምሩክ፣ ሲቪል አቬሽን የመሳሰሉትን መመስረት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ዜጎች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ አገልግሎት ማግኘት ሲጀምሩ ‹‹በቡድን ማሳብ፣ በዘር ማሳበብ እና መሰባሰብ›› እየቀነሰ ይመጣል፡፡  ይህ ካልሆነ ‹‹ቀን መራዘም›› እንጂ ‹‹ወደ ነገ ማዝገም›› የምንችል አልመሰለኝም፡፡

No comments:

Post a Comment