Friday, March 25, 2016

ለ "አንቺ ያለኝ ፍቅር"


ለፍቅርሽ ጥልቀት
ሰብዕናሽ ምጥቀት፤
ብራና ዳምጬ
ቃላትን መርጬ
ብዕሬን ጨብጬ፤
በሰከነ መንፈስ~ልፅፍ አስብና
ፈዝዠ እቀራለሁ~ሐሳብ ሁሉ መና
ማይጨበጥ ነፋስ~የቅዠት ደመና

ግራ ይገባኛል~ምን ላድርገው ደግሞ
ምባዬ ይፈሳል~ከብዕሬ ቀድሞ፤
ቃላትን ላጣምር~የያዝኩት ወረቀት
ቀለም እና እምባ~ አንድ ተዋህዶበት፤
ባህርን ይፈጥራል
መናኛ ሐሳቤም~ሰጥሞ ይጠፋኛል፤
ባህሩን አስሼ 
አድማስ አዳርሼ፤
አንካሳ ፊደላት~ቃላትን ልቆጥር
ስለ ፍቅርሽ ልፅፍ ብዬ ስጀምር፤
ደግሞ ወደ ውስጥ~ቁጣ ይሰማኛል
ብኩን ህሊናዬ~እንደዚህ ይለኛል፤
ምንስ ጠቢብ ብትሆን~ፊደላት ቢተርፉህ
ፍቅርን በቃላት~እንዴት ትገልፃልህ?”
እያለ ይለኛል
ግራ ይገባኛል፤

ግን እኮ አንቺን…….
ግን እኮ አንቺን…….
ቃላት ባይገልፁትም~የፍቅርሽን ጥልቀት
ልብሽ ባያውቀውም~የእምባዬን እውነት
አንድ እውነት ልንገርሽ
ካዳመጠኝ ጆሮሽ?
ፀሐ ብትጨልም~ከዋክብት ቢረግፉ
ምድር ባህሮች~አፍላጋት ቢነጥፉ
ሰማይ እና መሬት~ አንድ ቢዋሃዱ
ከሰማይሳት ወርዶ~ፍጥረታት ቢነዱ
ተፈጥሮ ቢከዳኝ~ሁሉም ቢቀያየር
ዘመን አይከስምም~ አንቺ ያለኝ ፍቅር
  ( አንቺ…. ታህሳስ 28 & የካቲት29 2008 .)

(ሳይኖሩ ለልጆቻቸው ለሚኖሩ ውድ ዓለም ጀግና እናቶች መታሰቢያ ይሁንልኝ)

No comments:

Post a Comment