Wednesday, March 30, 2016

በ እንተ “ማኅበረ ቅዱሳን”: ክፍል_2


 በ ፒዲኤፍ ለማንበብ ይህንን ይጫኑ


እውን ማኅበረ ቅዱሳን ለ ቤተክርስቲያን  ስጋት ወይስ አቃቤ?
በቤተክርስቲያኗ ህግ መሰረት ማህበረ ቅዱሳን ተፈቀደለት መስመር ከወጣ፤ መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አውጥቶ ማየትና የእርምት እርምጃ መውሰድ የሲኖዱሱ ጉባኤ ስልጣን ነው፡፡ ይህ ከሆነ ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተክርስቲያኗ ስጋት የሚሆንበት አንዳችም መንገድ አይታየኝም፡፡ ከዚህ ባለፈ ከ ሲኖዶሱ እውቅና ውጭ በተለያዩ አካላት “ሾላ በድፍን” የሚደረጉ ዘመቻዎች የምዕመናንን ሰላም ከማወክ ያለፈ የረባ  ፋይዳ ይኖራቸዋል ብዬ አላስብም፡፡ በሌላ በኩል ግን ጥንታዊ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ለማደስ በሚል ተልዕኮ በየቀኑ ለሚፈለፈሉ ምዕራብ ወለድ ሃይማኖቶች ከሆነ አሁንም ቢሆን ማኅበረ ቅዱሳን ስጋት ነው፡፡
ይህንን እውነታ እናድሳለን ባዮቹ እንደፈለጉ ገብተው እንዳይፈነጩ ማኅበሩ ደንቃራ እንደሆነባቸው በራሳቸው አንደበት መስክረዋል፡፡ በእኔ እይታ ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተክርስቲያን አቃቤ እንጂ ስጋት ይሆናል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምክንያቱም አገልጋዮቹ ለመንፈሳዊ ትሩፋት እንጂ ለስጋ ገባያ የገቡ ስላልሆኑ፡፡ ለስጋ ቢሆን ኑሮ የሚያጠፉትን ጊዜና ገንዘብ ወደራሳቸው ቢመልሱት የት ሊደርሱ እንደሚችሉ ለማንም የተደበቀ አይደለም፡፡
ይህንን እውነት በአንድ ወቅት ማኅበሩን ይጠሉ የነበሩትና የሰ//ቤቶች//መምሪያ ኃላፊ የነበሩት አባ ሰረቀ ብርሃን  እነ ዘማሪ ትዝታው ጋር ባደረጉት ውውይት ስለ ማኅበሩ እንዲህ የሚል ምስክርነታቸውን ቃል በቃል ሰጠው ነበር፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ውስጥ በአብዛኛው 70-80% በላይ የሚሆኑት ወጣቶችም እንበላቸው አሮጊቶች  መንፈሳዊ ፅናት የተነሱ መሆናቸው ይታያል፡፡ ይቅርና ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን፤ ህይወትህን ገብር ብትለው የሚገብር ትውልድ ነው እዚያ ውስጥ ያለው፡፡ እነሱን በቀላሉ ማስቆም ከባድ ነው10
 ብለው ባላንጣነትና ወዳጅነት የተቀላቀለበት ምስክርነት ሰጠው ነበር፡፡ አባ ሰረቀ እውነታቸውን ነው፡፡
ፈረንጅ ስለ ኢትዮጵያ ምዕመናን ሲጠየቅ የተናረው ትዝ አለኝ፡
የኢትዮጵያ ምዕመናን ደማቸው ቢመረመር ውስጡ ላይ ማርያም ማርያም ሚል ስም ይገኛልነበር ያለው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም እንደዚህ ነው፡፡ ከማንኛውም ግቢ ጉባኤ ከ ተመረቀ ወጣት ልብ ውስጥ ማኅበረ ቅዱሳን ተቀብሯል፡፡ ከማያውቀው ኢትዮጵያ ታሪክ ጋር፣ በስም እንጅ በውል ከማያውቃት ቤተክርስቲያን ጋር ያስተዋወቀውን፣ መንፈስና በስነምግባር ያነፀውን ማኅበር ማን ሊረሳ ይችላል? ሰው አንድ ቀን እንኳ አልፎ ሲሄድ የበላበትን ቤት እንዴት ይረሳል? እንኳን ዘላለማዊ ማዕድ ያቀረበለትን ቤት! ለዚህ እኔ ህያው ምስክር ነኝ፡፡ ምንም እንኳ በአሁኑ ሰዓት ምንም አይነት ሱታፌ የለለኝና የማኅበሩ ውለታ ባለዕዳ ብሆንም እውነቱን ለመካድ ግን ህሊናዬ አይፈቅድም፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ማንነት በመጠበቅ በኩል ያለውን ድርሻ፤ የ ዶክትሬት ዲግሪውን መመረቂያ ጥናት ዘጌ ገዳማት ውስጥ ያደረገው ቶም ቦይልስቶን እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፡  
Parachurch organizations such as the Association in the name of Saints (Mahibere Kidusan) have become key actors in the explicit assertion of Orthodox identities and values”11.
ከዚህ ባለፈ ማኅበሩን የሀገርም ስጋት አድርጎ የማሰብ አባዜዎችም አልፈው አልፈው ይሰማሉ፡፡ ምንም እንኳ የማኅበሩ ዓላማ ምድራዊ ባይሆንም በሃገር ፍቅር፣ በመንፈስና በስነ ምግባር የታነፁ ትውልዶችን ማፍራት በመቻሉና የበጎ አድራጎት ተግባራትን በመፈፀሙ ከመንግስትም ሆነ ከሌሎች አካላት እውቅና ሊሰጠው በተገባ ነበር፡፡
አርግጥ ህሊናውን እረግጦ፣ በፍቅረ ንዋይና በቁስ ስካር እራቁቱን በቆመ ዓለም ላይ ስለ መንፈስ፣ ስለ ስነ ምግባርና ስለ እውነት መለፍለፍ ድንጋይን ውሃ ከማጠጣት የከፋ ልፋት ነው፡፡ ቢሆንም ግን ሃቁን መሬት ውስጥ ቀብሮ፤ ስናፍጭን እንደ ተራራ አግዝፎ ማውራት በመጪው ትውልድ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ጥንታዊ ገዳማትንና አብነት /ቤቶችን የኔ ዘመን ትውልድ አልፍልጋቸውም ቢል እንኳ ለመጪው ትውልድ ያስፈልጋሉ፡፡ ምክንያቱም ታሪክን፣ እውቀትንና ሰማያዊ ተስፋን በውስጣቸው አርግዘዋልና፡፡ ይህ ደግሞ ከቤተክርስቲያኗ ባለፈ ለ ሃገርም ያለውን ፋይዳ ሰፋ አድ ጎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ትውፊታቸው ሳይበረዝ በ አሉበት እንዲቆዩ የሚታደግ አንድ ኅበር አይደለም ብዙ ሺህ ማኅበር ያስፈልጋል፡፡ ትውልዱ ወደ ራሱና ወደ ህሊናው ተመልሶ በሰከነ አዕምሮ ያለፈውንና የሚመጣውን ቆም ብሎ መቃኘት ያለበትም ይመስኛል፡፡ አሊያ፡
እንደ ነዱት መጓዝ እህያም አልበጀ
ሳር እበላ ብሎ ከጅብ ተወዳጀ
በሚለው ፈሊጥ የጅብ እራት ከመሆን መዳን የሚቻል አይመስለኝም፡፡
ማጠቃለያ
ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ቆም ብለው ነገሮችን የሚመረምሩበትን መንፈስ አምላክ እንዲያድላቸው ከመለመን ውጭ እሳቸውን ለመተቸት አቅሙም የለኝም፡፡ ምክንያቱም ነብዩ ዳዊት ቃል ያስረኛልና፡፡ አንድ ነገር ግን ላሳስባቸው፣ ከብዙ ዓመታት በፊት ለማኅበሩ የሰጡትን የፀና ምስክርነትና ሲመተ ፕትርክናቸው ማግስት የገቡትን ቃል ዞር ብለው እንዲያስታውሱ፡፡6,12
ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ በላይ በዙሪያቸው ያለውን ጭብጨባና ሹክሹክታ ወደ ጎን ትተው በፈሪሃ እግዚአብሔር በመንፈስ መፅናትና ጊዜውን መዋጀት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ፓትሪያርኩ ምንም እንኳ እንደ እኛ ስጋ የለበሱ፣ አንድ ነፍስ የያዙ ፍጡር ቢሆኑም ስለተቀበሉት የሚሊዮኖች ነፍስ አደራ ሲሉ ቆም ብለው ግራ ቀኙን መመርመር አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በራሳቸው አንደበት በተደጋጋሚ አምርረው ይጠሉት የነበረውን የብፁዕ አቡነ ጳውሎስን የአስተዳደር ዘመን እየደገሙ መሆናቸውን ሊገነዘቡት ይገባል፡፡13 ይህ ደግሞ የቆሰለችን ቤተክርስቲያን በእሾህ ከመውጋት አይተናነስም፡፡ 
ስለዚህ የቤተክርስቲያንን የአመራርና የአስተዳደር መዋቅር ማሻሻል፣ የጠቡትን ጡት የሚቆርጡ ሙሰኞችን መለዬትና እርምጃ መውሰድ፣ ስርዓተ ቤተክርስያንን መጠበቅና ማስጠበቅ፣ አብያተ ክርስቲያናትን ማስፋፋት፣ ምዕመናንን በሐይማኖትና በምግባር ማፅናት፣ የገጠር አድባራትንና ገዳማትን መንከባከብ፣ የአብነት /ቤቶችን ማጠናከርና መንከባከብ ቤተክርስቲያኗ ለነገ የማትለው ትልቅ የቤት ስራ መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ወርቅ የወለል ምንጣፍ በሚቀደስበት ሀገር ውስጥ፣ እራፊ ጨርቅና በኩራዝ የሚቀድሱ የገጠር ካህናትን ዞር ብሎ ማስታወስም ይገባል፡፡ ከዚህም አልፎ ቤተስኪያናቸውን ዘግተው ወደ ከተማ የሚኮበልሉ ካህናትን ባሉበት ለማቆየትም ቢሆን ጥረት መደረግ አለበት፡፡
ስለዚህ ፓትሪያርኩ አንድ ወቅት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጋርምኒልክመፅሔት ላይ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፡ ሰው ኃላፊ ነው በስልጣን ላይ የሚወጣ ሰው ለዘላለም አይኖርም ታሪክ ግን ዘላለማዊ ነው13 ብለው እንደተናገሩት፤ በሚያልፍ ዘመን የማያልፍ መልካም ስራ ሰርተው እንዲያልፉ አምላክ ይርዳቸው፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የዘመቱ የውጭ አካላትም ዓላማ ቤተክርስቲያኗንም በስሯ ያለውን ማኅበርም ከመንገዱ ሊያደናቅፉት አይገባም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንንም ከሜዳው ሊያወጡት አይገባም፣ ሚስማር ሊሆኑት እንጂ፡፡ ፈተናዎች የስራው ማረጋገጫ ሰርትፊኬቶች መሆናቸውን መገንዘብም ብልህነት ነው፡፡
ሃቅን  ከረገጡ እግዜርን  ከረሱ
ደቂቃ አያስተኛም የ  ህሊና  ክሱ
የሚለው የአዝማሪ ግጥም ሃይማኖት አባቶች የሚገባ ባይሆንም በስሜት ለምናጨበጭበው ለእኛ ለምዕመናኑ ግን እውነቱን በሰከነ መንፈስ መመርመርና መከተል ፅድቁ ቢቀር እንኳ ምድራዊ የህሊና ወቀሳና ጥፋት እንዲሁም ከታሪክ ተወቃሽነት ይታደገናል፡፡ ፅድቅ በውሸትና በማጭበርበር አይገኝምና፡፡ ትናንትን የሚመረምር፣ ዛሬን አስተውሎ የሚራመድ፣ ነገን የሚተነብይ የሰከነ አእምሮ ያድለን፡፡
                                               አሜን!
«የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው» ዕብራውያን 1378
(መሳሰቢ ፀሐፊው አሁኑ ሰዓት ከማኅበሩ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌለው መሆኑ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡)
                                    ã  መጋቢት 2008 .
ዋቢ ገጾች
10.  የአባ ሰረቀ እና እነ ትዝታው ውይይት፡ https://www.youtube.com/watch?v=wYdXW1NrSns
11.    Tom Boylston: The Shade of the Divine Approaching the Sacred in an Ethiopian Orthodox Christian Community; London School of Economics, PHD dissertation; march 2012:
12.   Patriarch Aba Mathias_ Interview with VOA: https://www.youtube.com/watch?v=X82Ek4ZHfQ8

13.  Who is Abune Mathias? What did he say on Eskinder Nega’s magazine 12 years ago?: http://www.awrambatimes.com/wp-content/uploads/abune-Mathias2001.pdf   

3 comments:

  1. ማህበረ ቅዱሳን ማህበርተኛ ለመሆን የአባል ፎረም መሙላት ግድ አስፈላጊ አይመስለኝም፣ ሳነናውቀው ሳናስበው ውስጣችን ማህበርተኛ ሁኖአል ። ፣ወስጣችሁን አንባችሁት ከሆነ ማህበሩ ሲያዝንና ሲደሰት የሜሰማውን ስሜት ፣ለማህበሩ ያለውን ፍቅርና አክብሮት ብሎም ታአማኔነት በቃላት የሜገለጽ ብቻ ሳይሆን በእንባም ጭምር ነው።ለዚህም መሰለኝ ይኸው ወንድሜ አይደለሁም እያለ ግን እንደ፣አብዛኞዎቻችን፣ሳያውቀው ትልቁ የልብ ውስጥ ማህተም የታተመበት መሆኑ ከጽሁፎ ያስታውቃል ።ማህበረ ቅዱሳን የታደለ ማህበር ነው ።አፋዌ ሣይሆን ልባዊ ማህበርተኛ በጣም ብዙ አለው ።ለዚህም እግዚአብሔር ይመስገን ።

    ReplyDelete
  2. ይህን አስተያየት የሰጠሁት 2016 ነው ።አሁንም እደግመዋለሁ ቃሌ ነው ፣ እግዚአብሔር ማህበሩን በፍቅር ጽናት ጸገ ይጠብቅልን ።አሜን!

    ReplyDelete