Wednesday, June 15, 2016

‹‹‹‹አዎ መምህር ነኝ!….›››

የትውልዱን ነገ ያዘልሁኝ ጀርባ
መጪውን እያሰብሁ ህልም የምባባ
አዎ መምህር ነኝ የእውቀት ደብተራ
ፈጣሪ በታች ሰውን የምሰራ

ጠመኔ ብናኝ በላጠው መዳፌ
መለፍልፍ ብዛት ደረቀ አፌ
ሰው ሃብታም የማደርግ ድህነት ታቅፌ
አዎ መምህር ነኝ
የእውቀት ደብተር እንጂ የባንክ ቡክ የሌለኝ

እንደ ደረሰች ሴት እውቀትን እያማጥሁ
ጠመኔ ታቅፌ ትውልድ ፊት የቆምሁ
ነገን እንዲሸከም ጮሄ የምሞግት
ደሞዝ ቀን የራቀኝ እንደ ዳግም ምፃት
አዎ መምህር ነኝ!
የመቶ ብር ምስል የሚያስደነግጠኝ

የቱጃር ቀበጦች የዋሌት ግልምጫ
ገንዘብ የሚያጋብስ ነጋዴ ሩጫ
ያላስበረገገኝ
ያላስደነበረኝ
ቁርሴን ተራምጄ ተማሪ ፊት ምገኝ
አዎ መምህር ነኝ!
እስትንፋስ ምዘራ ትንፋሽ እያጠረኝ

ለበስኩት ጃኬት ቢያልቅም ከጫንቃዬ
ሁለተኛ እግሬ ብታልቅም ጫማዬ
ምንም ቢቸግረኝ ከፊትህ ማልጠፋ
እውቀት አባትህ ነኝ ለነገህ ምለፋ

በል እንግዲህ ልጄ አስተውለህ ስማ
እኔ መምህር ነኝ በችግር ማልደማ
ካለው ወስዶ መስጠት
እጅ ይዞ ንፍገት
እንደዚህ ቢሆንም~ አለሙ አባዜ
ትርፌ አንተ ነህ ልጄ~አይደለም ደሞዜ
        ዘላለም፡ 2008 .
___________________________

(አበርክቶ፡ በትጋት ዳግም ለወለዱን መምህራን ሁሉ

No comments:

Post a Comment