Wednesday, June 22, 2016

......ሰበር ዜና…….

ኢትዮጵያ ካናዳ እርዳታ ሰጠች፡፡
ይህንን ዜና ዛሬ ማታ ተሜ ሲያነበው ብሰሙ ምን ትላላችሁ?…………………..ያው እውነትም አድገናል ማለት ነው ብላችሁ አገጫችሁን በእጃችሁ ተመርኩዛችሁ በመገረም መተከዛችሁ አይቀርም…….ፀረ ልማት ሃይሎች ካልሆናችሁ በቀር፡፡
..............
የሆነው ሆነና ኃይለ ስላሴ ዘመን ኢትዮጵያ ለካናዳ እርዳታ እንደሰጠች ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ? ……በኢትዮጵያ እርዳታ የተገነባውን የካናዳ ተቋምስ?

ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ያው እንግዲ 5ኛም አይደለሁ አለች ሻሸ፡፡ ......ያው እንግዲ መምህር መሆን ለዚህ ለዚህ ይጠቅማል፤ ለመረጃና ትናንትን ከዛሬ ጋር ለማገናኘት፡፡………………….ሰሞኑን ትንሽ ደረቴን አሳበጥሁ አይደል! ምን ላድርግ የደሞዝ ጭማሪውን በታሳቢነት እየበላሁ፡፡
…………….የደሞዝ ነገር ከተነሳ አይቀር አንዲት እህቴ………… ምነው ዘጋኸኝ…….ገና ብድር ትጠይቀኛለች ብለህ ፈርተህ ነው………………………ተወው ..ሞቼም አልጠይቅህ……………” አለችኝ፡፡ 
........
እኔ ምለው የሞተ ሰውም ይጠይቃል እንዴ……………ጉድ ሳይሰማ ሐምሌ ሊገባ ነውአሉ፡፡ ………..ጎበዝ አሁንስ ከሚጨመረው ገንዘብ በላይ የሚጠይቀኝ ሰው በዛ!
ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስ...ሰሞኑን የምስራቅ አፍሪካ መምህራን/ምሁራን በትምህርት ጥራት ላይ ለመወያየት እዚሁ አፍንጫችን ስር ( ኧረ አፍንጫችሁን አትዳሱ) ካለው የተ... አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ከትመዋል፡፡ (የትምህርት ጉዳይ ለሚመለከታችሁ ብቻ……ሌሎች ወደ ታሪኩ እለፉ)
እኔም የበኩሌን እንዳቅሚቲ ጥናት ቢጤ ለማቅረብ 14 ሀገራት በላይ ከተውጣጡ ምሁራን ጋር ተቀላቅያለሁ፡፡ የደሞዙ ልዩነት መሰለኝ እነሱ ወፈርፈር ወፈርፈር ያሉ ናቸው፡፡ ስብስባችን በተለያዬ ቀለም የተሳለ አብስራክት ይመስላል፡፡ ………….በእርግጥ መልክ ምን ያደርጋል ዋናው ጭንቅላት ነው ይላሉ አሉ ሴቶች፡፡
……….በእለቱ ንግግር እንዲያደርግ የተጋበዘው ሳይንቲስት ወደ መድረኩ ብቅ አለ፡፡ ፕሮፌሰር ብሬን ሆጄስ፡፡ ፕሮፌሰር ብሬን ካናዳ የሚገኘው የታላቁ የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ /ፕሬዘዳንት ነው፡፡ 
…………
ንግግሩን የጀመረው /ስላሴ ለካናዳ ያደረገውን እርዳታ በማውሳትና ምስጋና በማቅረብ ነው፡፡………………
……..እውነት ለመናገር ደነገጥሁ፡፡ ኢትዮጵያ እንግሊዝንና ህንድን አንደረዳች እንጂ ካናዳን እንደረዳች ከዚህ በፊት አላውቅም፡፡ …….አይ የእናንተ ነገር ይህንንም አናውቅም እንዳትሉ፡፡ ………..........ምን ታደርጉ ትናንታችን ላይ ውሃ ቸልሰን ፀሀይ የምንፈልግ ቅብዝብዝ ትውልዶችም አይደለን፡፡....... ፀሀይን ሰጠን ሻማ የምንለምን! ብዙ አታናግሩኝ፡፡
…………ቀዳማዊ /ስላሴ ካናዳን በተደጋጋሚ የጎበኙ ሲሆን በአንድ ወቅት ከታች ለምታዩት ዩኒቨርሲቲ ማሰሪያ የሚሆን አስር ሺህ ዶላር ($10000) እርዳታ አበርክተዋል (ብሩ ትንሽ እንዳይመስላችሁ …….ያኔ ካናዳ ደሃ ስለነበረች ይህ ብዙ ገንዘብ ነው፡፡).
......
ይህ ተቋም አሁን ሰድበሪ ዩኒቨርሲቲ ይባላል፡፡ በሃገሪቱ የባህል፣ የቋንቋና የፍልስፍና የልህቀት ማዕከል (center of excellence) ሆኖ ያገለግላል፡፡ ካናዳዊው ፍሬድሪክ ማቴ የቀዳማዊ /ስላሴ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ፕሬዘዳንት እንደነበርም በዚሁ ላስታውሳችሁ፡፡
…….......በእውነት ይህን ስሰማ ከጫንቃዬ ትንሽ ሸክም ቀለል አለኝ…………ለካስ የካናዳ ስንዴ ዝም ብሎ እርዳታ አይደለም…….ብድር ቅነሳ ነው፡፡ አንድ አኩል፡፡ መች ይሆን እኛ የአሜሪካን የምንመልሰው፡፡
……..የመረጃዎችን እውነትነት ለማረጋገጥ ጉግልን አናገርሁት፡፡ እሱም እውነት ነው ካላመንኸኝ ሳሂድ አድጆምቢ The history of Ethiopia ብሎ ... 2007 . ገፅ 178 ላይ የፃፈውን አንብብ አለኝ፡፡ ..አይ መምህር መሆን እቴ! ተረተርሁት!
…….እስኪ በነካ እጄ ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የረዳችውን ላረጋግጥ ብዬ ብነሳ ብወድቅ…….ጋሽ ጉግል እየገለበጠ ያወራልኝ ጀመር፡፡ ተስፋ ቆርጬ ተሁት፡፡ ምን አልባት አሜሪካኖች አጥፍተውት ይሆናል እንጂ ጃንሆይ ለካናዳ አስር ሲሰጡ ለአ ሜሪካ ትንሽ ሳይበጥሱ አይቀሩም፡፡
……ፕሮፌሰር ብሬን ምንአልባትም እኔ የማውቀን ያክል የኢትዮጵያን ታሪክ ያውቃል፡፡ በተለይ ዮዲ አቢሲንያ በነበረን ምሽት እጅግ የሚገርሙ ታሪኮችን አጫውቶኝ ነበር፡፡ 
.............
ፕሮፌሰሩ ሁሌም ጥናት ሲያቀርብ ከጥናቱ መጨረሻ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር (በእንግሊዝኛ መሆኑን አትርሱ) ከሚለው ፅሁፍ ጀርባ የላሊበላን ውቅር ቤተመቅደስ ፎቶ ያሳያል፡፡ ለምን ብዬ ጠየቅሁት........
.......
. የላሊበላ ኪነ ህንፃ ሰው በህብረት ካልሰራ በቀር በፍፁም ሊታሰብ የሚችል አይደለም፡፡ ይህ ህንፃ ለኢትዮጵያውያን የታላቅ ህብረት ምስጢር ነው አለኝ፡፡ ………..አንገቴን ደፍቼ ትንሽ ተከዝኩና ካናዳን መርዳታችንን ሳስብ ቃና አልኩ፡፡……ይሄ ነጭ መች የቤታችንን ጉድ አወቀ፡፡ .........ለማንኛውም ታላቅ ህዝቦች ነበርን፤ ታላቅም እንሆናለን!………. ሸገር ሬዲዮ ጣቢያ መሰለ አይደል……
......
ግን መቼ ነው ታላቅ የምንሆነው???..አሁንስ ምንድን ነን???
ይቅርታ ከመውጣታችሁ በፊት አንድ አሳይመንት፡ እስኪ በነካ እጃችሁ በኢትዮጵያ የተረዱ ሌሎች አገሮችን እባካችሁ እባካችሁ ጀባ በሉኝ፡፡

                            መልካም የታላቅነት ዘመን!

1 comment:

  1. ኧረ.......እንዴት ደስ የሚል ታሪክ መሰላችሁ...ለካ ይህም አለ??እኛማ የቤት አይጦች ምኑን አውቀነው.......ኧረ እባካችሁ አሁንም ከእናንተ ብዙ ነገር እምጠብቃለን......ልክ እንደ "ይድረስ ለባራክ ኦባማ"........

    ReplyDelete