Monday, June 27, 2016

ቃና ከውስጣችን አልፎ ት/ቤት ውስጥ ገባ….

“ቃና ውስጤ ነው” የሚለው አረፍተ ነገር  ትርጉም ከማይገባቸው ሰዎች ተርታ ውስጥ ነኝ፡፡ አሁን ግን ትርጉሙ ትንሽ ትንሽ የገባኝ ይመስለኛል፡፡ …………..ማንነትህን ቃና ቲቪ ላይ በምታየው ነገር መቀየር ከሆነ ትርጉሙ ገብቶኛል፡፡

…….በ አንድ ወቅት በ እውቀቱ የፌስቡክ ሱስን በተመለከተ “በረከተ መርገም_2” በሚለው ግጥሙ የፌስቡክን ፈጣሪ የወረፈበት ግጥም ትዝ ይለኛል፡፡ ለቃና “በረከተ መርገም_3” መግጠም ብዙ የሚከብድ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ከፌስቡክ በላይ ከ ህፃን እስከ አዛውንት ሁሉም የቃና እስረኛ ስለሆነ፡፡ እነሆ ቃና ከመጣ የቤት ስራውን ሳይሰራ ት/ቤት የሚሄድ ተማሪ ፣ ራት ሳትሰራ የምትቆይ እማዎራ፣ ራቱን ሳይበላ የሚተኛ አባወራ (ምን እራቱን ብቻ ነገርዮውን ረስቶ ሶፋ ላይ ተዘርሮ የሚያድር)፣ መድሃኒቱን እረስቶ የሚተኛ ህመምተኛ፣ ሲኒማ ለምኔ የሚል ፍቅረኛ እየተበራከተ መጥቷል፡፡

ማንም ቢሆን ከሌላው አገር ስልጣኔን መማር የሚጠላ የለም፡፡ እኔም ብሆን አልጠላም (የትናት ናፋቂ የሚል ሰሌዳ እንዳትለጥፉ)፡፡ ግን ማንነትን የሚውጥ፣ ስምን የሚለውጥ ስልጣኔ ለእኔ ስልጣኔ ሳይሆን ስንጣኔ ነው፡፡

ቃና በትክክል ውስጣችን መግባቱን ሳይውል ሳያድር ይኸው ት/ቤት ውስጥ አየነው፡፡ እነሆ “ቃና ውስጣችን ነው” ብለው የተቀበሉ የ ኬጂ መምህራን ህፃናትን ቃና ውስጥ በሰሟቸው ስሞች ማጥመቅ ጀመሩ፡፡ ………በልጅነታችን ከፊደልና ከንባብ ጋር የተዋወቅንባቸው…. “ጫልቱና ቶሎሳ”፣ “ዛራና ቻንድራ በሚል ተተኩ”፡፡ በዚህ ከ ቀጠለ ወደ ፊት……. “ኦማር በሶ በላ”፣ “መቲ ጩቤ ጨበጠ”፣ “ኤሊፍ ወደ ት/ቤት ሄደች” የሚሉ ምሳሌዎች የቋንቋ ማስተማሪያ መፅሃፍት ውስጥ መኮልኮላቸው አይቀርም፡፡ እነ “አበበ፣ ከበደ፣ ጫላና ጨቡዴ” እንደ አክሱምና ላሊበላ ከ ቅርስነት አያልፉም፡፡  

ገና ካሁኑ በርና፣ ኦማር፣ ኦሊሳንድሮ የመሳሰሉ ቅፅል ስሞች በየሰፈሩ በርክተዋል፡፡ ነገ ልጆቻችንን በነዚህ ስሞች ላለመሰየማችን ምን ዋስትና አለን? የማንነት ድንበርስ እስከየት ነው? እውን እኛ ለምሳሌ የሚሆን ስም እንኳ የሌለን ህዝቦች ነን?

በእርግጥ በነፃ ገባያ ስርዓት ማንም ሰው ያዋጣኛል የሚለውን ንግድ መክፈትም መዝጋትም ይችላል፡፡ ያም ቢሆን ግን ሀገሪቱ ባህሏንና ቋንቋዋን መከላከልና መጠበቅ የምትችልበት በር አልተዘጋም፡፡ ፍላጎቱ ካላት፡፡ ተርጉመው የሚያቀርቡት ሰዎችም ቢሆን የእኛው ጉዶች ስለሆኑ ቢያንስ ስማቸውን አገረኛ ቢያደርጉት ዘላቂ ባይሆንም ጊዜያዊ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ በተረፈ እያደረጉት ያለው ነገር የ እጂ አዙር ቅኝ ግዛቱ አካል መሆኑን አጠንክሬ ልነግራቸው እወዳለሁ፡፡ ያልተነካ ቱባ ባህል፣ ዘመን የማየይሽረው ታሪክ፣  የሚያማልል መልካዓምድር፣ ያልተዘመረለት ማንነት በውስጧ በታቀፈች አገር ውስጥ ለድቃቂ ሳንቲም ብሎ የምዕራባውያንን ባህል ማስረፅ ከ አገር ክህደት በምንም አይሻልም፡፡


       …………..ቃናዎች ልለምናችሁ፤ እባካችሁ ስማችንን እንኳን ተውልን፡፡ 

1 comment: