Friday, March 31, 2017

(‹ያለመቻል ግጥም››)

ልፅፍልሽ ብዬ፡
እንደ ገዳም መናኝ ቀልቤን ስሰበስብ
ለ አንቺነትሽ ቅኔ ገላጭ ቃላት ሳስብ
እንደ ርደ-መሬት ትዘላለች ልቤ
ፅሞናዬ ጠፍቶ ይበተናል ቀልቤ
‹‹ ፈዝዤ እቀራለሁ››
ጎንበስ ብሎ መፃፍ ተስኖት ወገቤ

ልፅፍልሽ ብዬ፡
የ እናቱን ሞት ሰምቶ እንደ ደነገጠ
በድን እንደሆነ ሞት እንደ ጨበጠ
ማሰብ ይሳነኛል ቃል ይጠፋል ካፌ
ብዕር መያዝ ከብዶት ይዝላል መዳፌ፤

የት ሄደ ግዝፈቴ
የት ሄደ ሐሞቴ
ወዴት ነው ድፍረቴ
………‹‹ብቻዬን የቀረሁ››
ታውቂ እንደሁ መልሽ..‹‹እኔ ምን አውቃለሁ››

ልፅፍልሽ ብዬ፡
ሰማይን አስሼ
አድማስ አዳርሼ
ከ ቤተስኪያን ታዛ ቅዳሴ አስቀድሼ፤
አስኳላ ቅኔ ቤት ሰርክ መንከራተቴ
ለ አንቺ ጊዜ ሲሆን ይከስማል እውቀቴ
ልፅፍልሽ ብዬ፡
ከዚህ ሁሉ አልፌ
ከ ቀን ተጣልቼ ከ ቀን ተኳርፌ
በ ስምሽ ቃዥቼ ስነቃ ከ እንቅልፌ
የ ኪራይ ግድግዳ በ ሃሳብ ተደግፌ
እንደ ምስረታ ቤት ቀልቤን ሰባስቤ
አስቤ አስቤ አስቤ አስቤ….
‹‹በ ዝርው በግጥም መፃፍ ብሞክርም
ለ ካስ ቃል ሽባ ነው ስሜትን አይገልፅም››
ኤጪጪጪጪ………….

እንግዲህ ምን ላድርግ፡
የ አምሮዬን ጫጫታ
የ ህሊናን ዋይታ
የ ልቤን ትርታ
የ ነፍሴን ስቅታ
ቢገልፅም ……ባይገልፅም
ተቀበይ ልኬያለሁ ‹‹ያለመቻል ግጥም››
( ለ አንቺና ለ አንቺ ብቻ)



No comments:

Post a Comment